በጋምቤላ ክልል በግብርና እና በማዕድን ዘርፎች ለወጣቶች የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት እየተሰራ ነው

27

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 23/2015 በጋምቤላ ክልል በመጪዎቹ አምስት ወራት በግብርና እና በማዕድን ዘርፎች ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ኦባንጉ ጉታዱ ገለጹ።

የክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ኦባንጉ ጉታዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ለወጣቶች የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ስድስት ወራት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ከ9 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተመቻቸላቸው ነው ያስረዱት።

ክልሉ በድጋፍ ያገኛቸውን 36 የእርሻ ትራክተሮችና 150 የውኃ መሳቢያ ጄነሬተሮች በግብርና ዘርፍ ለተደራጁ ወጣቶች ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉ በክልሉ ያለውን ሰፊ መሬትና የውኃ ኃብትን በመጠቀም ወጣቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የግብርና ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የሚያግዝ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በቀጣይም በተለይም በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢንተርፕራይዝ ለተደረጁ ወጣቶች ያለባቸውን የፋይናንስ ችግርን ለመፍታት የብድር አቅርቦት ከተለያዩ ባንኮች ጋር በመሆን እየተመቻቸ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የተደራጁ ወጣቶችን የክህሎትና የሥራ ሃሳብ የማበልጸግ ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

በተለይም የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ተቋም (ጂ. አይ. ዜድ) ጋር በመተባበር በክልሉ ከሚገኙ ሁለት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን ግብዓት የማሟላትና የማደራጀት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወርቅ በብዛት በባህላዊ መንገድ በሚመረትበት ዲማ የሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በወርቅ አመራረት ዘርፍ ሥልጠና ለመስጠት አዲስ የትምህርት ክፍልና የአሰልጣኞች ቅጥር መፈጸሙንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ ሦሰት ኮሌጆችን ለመክፈት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወጣቶችን ወደ ሥራ ማስገባት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደጉም በላይ ለሰላምና ጸጥታ መረጋጋት አስፈላጊ በመሆኑ ከሌሎች አካላት ጋር የተጀመረው የቅንጅት ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም