በኦሮሚያ ክልል በበጋ መስኖ ልማት ስራ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑ ተገለጸ

206

አምቦ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 በኦሮሚያ ክልል በበጋ መስኖ ልማት ስራ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑ ተጠቆመ።

በኦሮሚያ ክልል በበጋ መስኖ ልማት የታየውን በጎ ጅምር የበለጠ በማጠናከር ውጤታማ ስራ ይሰራል ሲሉ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ማሕበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ ገለጹ።

በምእራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት እስካሁን ድረስ ከ72 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ መልማቱ ተገልጿል። 

አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ በዞኑ በወልመራ ወረዳ ቀርሳ ቀበሌ 545 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም የለማ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ጎብኝተዋል፡፡ 

አቶ አብዱልሃኪም በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት በመስኖ ስንዴ ልማት ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን የማስፋት ስራ ይሰራል። 

ከዚህ ጎን ለጎን በበጋ መስኖ ልማት ስራው የተስተዋሉ ችግሮችን በማረም ልማቱን ተስፋፍቶ እንዲቀጥል ይደረጋል ነው ያሉት። 

በክልሉ እየተካሄደ ያለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ምርታማነትን በእጥፍ እየጨመረ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የዞኑ አርሶ አደሮችም በተለይ የበጋ መስኖ ስንዴን በኩታገጠም በማልማት የጀመሩትን ጥረት የበለጠ እንዲያጠናክሩ አቶ አብዱልሀኪም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወራት እስካሁን ድረስ ከ72 ሺህ 66 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ ለምቷል። 

ከዚህም 3 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

አርሶ አደር መላኩ ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት በክረምት ወቅት የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በፈሰሰበት መሬት ላይ የበጋ ስንዴ አልምተው ምርቱ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

ሌላው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር መቃሳ አበበም እንዲሁ በክረምት ወቅት የአዋሽ ወንዝ መሬቱ ላይ ተኝቶ በበጋ ወራት ምንም የማይሰራበት መሬት ላይ የባለሙያ ምክርና ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ስንዴን በመስኖ በመዝራታቸው መደሰታቸውንና ጥሩ ምርት እንደሚጠብቁ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል እስካሁን በተከናወነ የበጋ መስኖ ልማት ስራ ከአንድ ሚሊዬን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም