የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ስድስት ወራት አፈጻጸም ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ተስፋ የሰጠ ነው - ሚኒስትሮች

27

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ስድስት ወራት አፈጻጸም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ተስፋ የሰጠ መሆኑን ሚኒስትሮች ገለጹ።

በቀጣይ በአፈጻጸሙ የታዩ መልካም ጎኖችን ማስቀጠልና የተስተዋሉ ድክመቶችን ለማረም በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የገበታ ለአገር ፕሮጀክት አካል በሆነው ሐላላ ኬላ ተካሂዷል።

በመድረኩም በዘንድሮው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚያድግ ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸም ማመላከቱ ነው የተገለጸው።

ከዘርፎች አፈጻጸም መካከል ግብርና በተለይ ደግሞ በሰብል ልማት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡ ተጠቁሟል።

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለጹት፤ ዘርፉ አሁንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት መሆኑን ይናገራሉ።

ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችና ተሞክሮዎች ተቀርጸው ወደ ሥራ በመገባቱ ለውጥ መታየቱን ጠቁመዋል።

ዘርፉ ለዚህ ደረጃ እንዲበቃም በመንግሥት በኩል በርካታ ማበረታቻዎች መደረጋቸውን ጠቁመው፤ መካናይዜሽን እንዲስፋፋና ዘርፉ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም በማድረግ ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በዘርፉ እንደ አገር ተስፋ የሚሰጥ የሚቆጠር ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ በተለይ የኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ አምራች ዘርፉን ማነቃቃቱን ተናግረዋል።

በግማሽ ዓመቱ ስድስት አዳዲስ ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ መግባት መቻላቸውን ጠቁመው፤ በዚህም ከዚህ ቀደም ያልታዩ ገበያዎች ጋር መድረስ መቻሉንም ገልጸዋል።

ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት በተሰራው ሥራም አንዳንድ ምርቶችን ከመተካት ባለፈም ወደ ውጪ መላክ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፣ በግማሽ ዓመቱ የትምህርት ሥርዓቱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያመላክት ውጤት የተገኘበት እንደነበር ገልጸዋል።

በቀጣይም ከችግሩ በመነሳት ዘለቄታዊ መፍትሄን ለማስቀመጥ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ጠንካራ ሥራ በመሰራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በስድስት ወራትም 100ሺህ ቤቶችን በግል ሴክተሩ አስተባባሪነት ለመገንባት ታቅዶ 80 ሺህ ቤቶች መሥራት መቻሉን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በገበታ ለአገር አካል በሆነው ሐላላ ኬላ የተካሄደው የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም