በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመድገም እየተሰራ ነው - የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመድገም እየተሰራ ነው - የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ

አዳማ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመድገም እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ እንዳሉት የንቅናቄ መድረኩ ዓላማ በግብርና ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች በኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም ለመድገም ያለመ ነው።
ጥሬ የግብርና ምርቶችን በመላክ ከውጭ የምናስገባውን የፍጆታ ዕቃዎችና ሸቀጦች በሀገር ውስጥ መተካት ይገባል ይገባል።
በክልሉ ያሉ ባለሃብቶችና የኢንቨስትመንት ተቋማትም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄውን ዕውን በማድረግ ዘርፉን መደገፍ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት 101 ስራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ዳግም ወደ ምርት መግባታቸውን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ ከዚህ ውስጥ 53 የሚሆኑት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ናቸው ብለዋል ።
በተመሳሳይ 634 አዳዲስ የማኑፋክቸሪንግና የኢንቨስትመንት ተቋማት ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ምርት እየገቡ መሆናቸው የንቅናቄው ውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል።
የተቀናጀ የብድር ፓኬጅ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ስራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ግቡን እንዲያሳካ በ168 ወረዳዎች ላይ ያሉ የማኑፋክቸሪንግና የኢንቨስትመንት አማራጮች በጥናት በመለየት የጎጆ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም ሃላፊው ገልጸዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎችን እየተፈታተኑ ያሉ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች፣ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥና የአቅርቦት ማነቆዎችን ለመፍታት አሁንም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ-ጉባኤ አቶ ኤሊያስ ዑመታ እንዳሉት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ምክንያቶች ማምረት ያቆሙ አነስተኛ፣ መካከለኛና ትላልቅ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችዳግም ወደ ማምረት እንዲገቡ ያስቻለ ነው።
በኦሮሚያም በተለያዩ ምክንያቶች ማምረት ያቆሙ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረገላቸው ድጋፍና ማነቃቃት ዳግም ወደ ስራ በመግባት ውጤታማ እየሆኑ ነው ብለዋል።

በተለይም በግብዓት አቅርቦትና ጥሬ ዕቃዎች እጥረት፣ በውጭ ምንዛሪና የመሰረተ ልማት ችግሮች ስራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ምርታማነት እንዲመለሱ ያስቻለ በመሆኑ አሁንም ንቅናቄው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።
በተለይም ከአሰራርና የህግ ማዕቀፎች ጋር ተያይዞ ያሉትን ማነቆዎች ለመፍታት ጨፌው ተገቢውን ድጋፍ፣ ክትትልና ዕገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው ንቅናቄው የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ የስራ ፈጠራን ለማበረታታትና ለማብቃት እንዲሁም የዕደ ጥበብ ስራን ለመደገፍ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

መስተዳድሩ ለአምራችና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ስምንት ጽሕፈት ቤቶችን በአንድ ላይ የያዘ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አክለዋል።
በዚህም አመቺ የሆኑ ፈጣንና ቀልጣፋ የዲጂታል አገልግሎት፣ የመሬት አቅርቦትና ተገቢውን ደጋፊና ዕገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባው አክለውም መሬቱን አጥሮ በማስቀመጥ ለሶስተኛ ወገን ለማስተላለፍና በአቋራጭ ለመበልጸግ ጥረት እያደረጉ ያሉ ባለሃብቶች ላይ መስተዳድሩ እርምጃ ይወስዳል ብለው፤ በተጨማሪም ግንባታ ገንብተው ለማከማቻ መጋዘን የሚያከራዩ አካላት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ጨርቃጨርቅ፣ የጎጆ ኢንዱስትሪና ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረገና ለዚህም የአስር ዓመት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱ ይታወሳል።