ቀጥታ፡

በጉባዔው አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተሳታፊዎች ገለጹ

ሀዋሳ መስከረም 24/2011 ከኢህአዴግ 11ኛው ጉባዔ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ የጉባዔው ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት ተሳታፊዎች ጉባዔው የሰብዓዊ መብቶችን ጨምሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለን እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢህአዴግ ጉባኤ በመሳተፍ መደሰታቸውን የተናገሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተርና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ በጉባዔው  ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎች ይተላለፉበታል ብዬ እጠብቃለሁ ነው ያሉት፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር ዐብይ አህመድ በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ጠንካራና ወደ ተግባር ሊቀየር የሚችል ንግግር መሆኑን የተናገሩት አቶ ኦባንግ በጉባኤው ማጠቃለያም ጠቃሚ የሆኑ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በጉባዔው መክፈቻ ላይ የቀረበው ሙዚቃዊ ድራማ አንድነትንና ኅብረ ብሄራዊነትን እንደሚያሳይ የተናገሩት አቶ ኦቦንግ ሙዚቃዊ ድራማው እኛ ያጣነው ነገር በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ወደፊት መጓዝ እንጅ ወደ ኋላ መመለስ አይገባም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ተስፋ የሚሰጠውና ወደፊት እንድናይ አመላካች የሆነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉባዔው መክፈቻ ንግግር ከጉባዔው ብዙ እንድንጠብቅ አድርጎናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ጉባዔው የዜጎች ሰብዓዊ መብት የሚከበርበት እንዲሁም ግጭትና አለመግባባቶችን  የሚፈታ  ውሳኔና አቅጣጫ ይቀመጣል ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት በመከበሩ ሁሉም ማንነቱን እንዲያስተዋውቅ እድል ያገኘበት መሆኑን የገለጸው  የደቡብ ኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር አባል ድምጻዊ ክፍሌ ወሰኔ ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለው ችግር በአስቸኳይ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚገባ የጠቆመው ድምጻዊው ጉባዔው ለችግሩ እልባት የሚሰጥ ውሳኔ እንደሚጠብቅ ተናግሯል፡፡ በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳቶች መድረሳቸውን ያስታወሱት የደቡብ ኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር መሰራችና ሊቀመንበር ድምጻዊ ወንድዬ አበበ በበኩሉ  ለችግሮች ምክንያት የሆኑ  ነገሮችን ሊያስወግድ የሚችል ውሳኔ ከጉባዔው እጠብቃለሁ ብሏል፡፡ ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች ያለምንም ስጋት ተንቀሳቅሰዉ የሚሰሩበትና የሚኖሩበት ብሎም አስተማማኝ ሰላም  የሚያሰፍን አቅጣጫ በጉባዔው ይቀመጣል ብሎ እንደሚጠብቅ ገልጿል፡፡ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው በ11ኛው የኢህዴግ ጉባኤ ከሁለት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም