13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊ ክለቦች ድልድል ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊ ክለቦች ድልድል ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ መስከረም 24/2011 13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊ ክለቦች ድልድል ይፋ ሆነ። በዚህ ውድድር በከተማዋ ከሚገኙት ሶስት ክለቦች በተጨማሪ በተጋባዥነት ከክልል እግር ኳስ ክለቦች ፋሲል ከነማ፣ ወላይታ ዲቻ፣ ጅማ አባጅፋርና አዳማ ከተማ ተሳታፊ ይሆናሉ። ከዚህ በተጨማሪ ኳራ ዩናይትድ የተባለው የናይጀሪያ እግር ኳስ ክለብ እንደሚሳተፍ ተገልጿል። በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ዋንጫ ስምንት ክለቦች የሚካፈሉ ይሆናል። ጨዋታው በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚደረግ ሲሆን በምድብ ''ሀ'' ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና አዳማ ከተማ ተደልድለዋል። በምደብ ''ለ'' ደግሞ ፋሲል ከነማ፣ ወላይታ ዲቻ፣ ኳራ ዩናይትድና ጅማ አባጅፋር ተደልድለዋል። ውድድሩ በመጪው ቅድሜ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓም የሚከናወን ሲሆን በመክፍቻው እለት በሚካሄዱት ሁለት ጨዋታዎች መከላከያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ። የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው ይህ ውድድር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ክለቦች አቋማቸውን ለመፈተሽና ያለባቸውን ችግር ለመለየት የሚያስችል ውድድር ነው።