የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የአውሮፓ ህብረት የቢዝነስ ፎረም በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የአውሮፓ ህብረት የቢዝነስ ፎረም በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የአውሮፓ ህብረት የቢዝነስ ፎረም በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የአውሮፓ አባል ሀገራት ባለሀብቶች በጋራ መስራት የሚያስችላቸው መሆኑም ተገልጿል፡፡
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሃመድ የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማሻሻልና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የ10 ዓመት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጅዎችን በምትቀርጽበት ወቅት የቢዝነስ ስራዎችን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ እንደነበረው ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ተቀዳሚና ተመራጭ የቢዝነስ መዳረሻ ለማድረግ ከህብረቱ ጋር በትብብር እንሰራለንም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ የግብዓት፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የገበያ ትስስር፣ የመሰረተ ልማትና የመሬት አቅርቦት ችግርችን በተቀናጀና በተናበበ መንገድ በመፍታት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ለማሳደግ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአውሮፓ የቢዝነስ ፎረም ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍና አምራች ኢንዱስተሪውን ለማሻሻል በርካታ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ በሁሉም አባል ሀገራት እንዲላኩ በማድረግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታገኝ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በመድረኩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ መልካም እድሎች፣ ችግሮችና የፖሊሲ የመፍትሔ አማራጭ ሀሳቦችን የያዘ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡