የአገው ፈረሰኞች የፅናትና ጥንካሬ ተምሳሌት ናቸው - ዶክተር ይልቃል ከፋለ

98

እንጂባራ (ኢዜአ ጥር 23/2015) … የአገው ፈረሰኞች የፅናትና ጥንካሬ ተምሳሌት በመሆን ለአሁኑ ትውልድ ታላቅ ትምህርት የሚሰጡ ናቸው ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለፁ።

የአገው ፈረሰኞች ማህበር 83ኛው ዓመት የምስረታ በዓል በታላቅ ፌስቲቫል በእንጂባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በፈረሰኞች ፌስቲቫሉ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል በወቅቱ በነበረው የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል አባቶቻችን የከፈሉትን መስዋእትነት የሚዘክር ታላቅ ክብረ በዓል ነው።

ፈረስ በፀረ ቅኝ ግዛት ወቅት ተዋጊዎችን፣ የጦር መሳሪያ፣ ስንቅና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ አባቶቻችን ላስገኙት ድልና ላቆዩት ሉዓላዊነት የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል ብለዋል።

በተጨማሪም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ወደ ኋላ በመመለስ በወቅቱ እንደ አምቡላንስ ሆኖ አገልግሏልም ብለዋል።

ይሄን የፈረስ አስተዋፅኦና የአባቶቻችንን ጀግንነት ለመዘከር ደግሞ የአገው ፈረሰኞች ማህበር ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 83 ዓመታት በዓሉን በማክበር ዛሬ ላይ መድረሱ የፅናት ተምሳሌት ያደርገዋል ነው ያሉት።

ዶክተር ይልቃል አክለውም ማህበሩ በተለያየ ጊዜ የሚገጥሙትን ችግሮችና ውጣውረዶችን ተቋቁሞ ለዛሬው የደመቀ በዓል አከባበር መብቃቱም ለአሁኑ ትውልድ የፅናት አብነት ያደርገዋል ብለዋል።

እኛም አቅደን በምንሰራቸው የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ስራዎቻችን የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች ተቋቁመን በመፈፀም የብልፅግና ጉዟችንን ልናረጋግጥ የሚያስችል ትምህርት ያገኘንበት ነው ብለዋል።

ይሄን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኘውን ፌስቲቫል በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ለአገራዊ ጥቅም ለማዋልም የክልሉ መንግስት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስረድተዋል።

የአገው ፈረሰኞች ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን የምዝገባ ሰርቲፊኬት ማግኝቱም ተጠቁሟል።

በዓሉ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ፈረሰኞች፣ እንዲሁም በርካታ እንግዶች በባህላዊ ልብስ አሸብርቀው በተገኙበት በተለያዩ ትርኢቶች በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም