ከንቲባ አዳነች አቤቤና ካቢኔአቸው በዴንቨር ከተማ ከንቲባ ለተመራው ልኡካን ቡድን አቀባበል አደረጉ

48


አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2015፦ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤና ካቢኔአቸው በዴንቨር ከተማ ከንቲባ ለተመራው ልኡካን ቡድን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቀባበል አደረጉ።

ረዥም ዘመንን ያስቆጠረው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት በከተሞች መካከል በሚደረግ የእህትማማች ግንኙነት ይበልጥ እንደሚጠናከር ከንቲባዋ ለልዑካን ቡድኑ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል።


የአፍሪካ ዋና ከተማና ከኒውዮርክና ጄኔቫ ቀጥሎ 3ኛዋ የዲፕሎማቲክ ማዕከል ወደሆነችውን አዲስ አበባ እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት ከንቲባ አዳነች በውቢትዋ አዲስ አበባ ጉብኝታችሁ የህዝባችንን እንግዳ ተቀባይነት ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ሁኔታ ትመለከታላችሁ ብለዋል፡፡

አዲስ አበባና ዴንቨር ከተማ የእህትማማችነት ግንኙነትን በማጠናከር በባህል፤ በትምህርት በኢኮኖሚ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት አስተዳደሩ ያለው ቁርጠኝነት የሁለቱን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡


አዲስ አባባ ከ27 ያህል የዓለም ከተሞች ጋር የእህትማማቾች ስምምነት ተፈራርማ የባህልና የንግድ ትስስርን ለማጠናከር እንደምትሰራ የገለፁት ከንቲባ አዳነች ከዴንቨር ከተማ ጋር በተመሳሳይ የእህትማማችነት ስምምነት እንደሚፈፀም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ዴንቨር በርካታ ኢትዮጵያውን የሚኖሩበት ከተማ መሆኑን ያወሱት ከንቲባዋ ይህም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በከተሞቹ መካከል የሚጀመረው በረራ የእህትማማችነት ግንኙነቱን ይበልጥ የሚያጠናክረው መሆኑን አስረድተዋል።


የዴንቨር ከተማ ከንቲባ ማይክል ቢ ሀንኮክ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ ለተደረገላቸውን ደማቅ አቀባበል እጅግ አመስግናለሁ ብለዋል፡፡


ከንቲባው የአፍሪካ መዲናና እናት ምድር ወደሆነችው አዲስ አበባ መምጣት ታላቅ ክብር መሆኑን ገልጸው ለመጪው ትውልድም ውርስ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡


ለ2ኛ ጊዜ አዲስ አበባ መምጣታቸውን የገለፁት ከንቲባው ዛሬም 22 የተለያዩ የስራ ሃላፊዎችን አዲስ አበባ ይዘው ለመምጣታቸው ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ዴንቨር ከተማ በረራ እንዲኖር በማስቻል፤ በባህል፤ ቱሪዝምና ትምህርት መስኮች በሁለቱ ከተሞች መካከል ትስስሩን ለማጠናከር እንደሆነ አስረድተዋል።


ከተማቸው ዴንቨር የከተማውን ባህል፤ ቱሪዝም፤ ኢኮኖሚ ከሌሎች ዓለማት ጋር በማስተሳሰር በተለይም የአፍሪካ ዋነኛ መግቢያ በር የሆነችውን አዲሰ አበባን በመጠቀም ከሌሎች አፍሪካዊያን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግም ጭምር እንደሆነ ከንቲባ ማይክል ቢ ሃንኮክ ገለጸዋል ፡፡


ከንቲባ ማይክል ቢ ሃንኮክ በከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባን ዳግም እንዲጎበኙ ለቀረበላቸው ግብዣ ማመስገናቸውንም ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም