በአማራ ክልል ቅርሶችን በማስተዋወቅ ቱሪስትን ለመሳብና የሃብት ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው---የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ

15

እንጅባራ (ኢዜአ) ጥር 22/2015---በአማራ ክልል የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በማልማት፣ በመጠበቅና በማስተዋወቅ ቱሪስትን ለመሳብና የሃብት ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

የአገው ፈረሰኞች ማህበር የ83ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የፈረሰኞች የሙዚቃ ፌስቲቫልና የልጃገረዶች የቁንጅና ውድድር በእንጅባራ ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ክልሉ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች መገኛ ነው።

የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፣ የፋሲል ግንብ፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጣና ሐይቅ፣ የዓባይ ወንዝ መነሻ፣ የጢስ ዓባይ ፏፏቴና ሌሎች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶች መገኛ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በማይዳሰስ ቅርስነት የሚታወቁት እንደ ጥምቀት፣ መስቀልና ሌሎች ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ቱሪስትን ለመሳብ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለሃብት ምንጭነት ለማዋል እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የአገው ፈረሰኞች በዓል በውስጡ በርከታ እሴቶችና ትውፊቶችን መያዙን አስታውሰው፣ በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ለማድረግና የአገርን ገጽታ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በአማራ ክልል የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኘው በበኩላቸው፣ የአገው ፈረሰኞች ማህበር በኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን የምዝገባ ምስክር ወረቀት ማግኘቱን ገልጸዋል።

"ይህም በቀጣይ በዓሉን በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት በማስመዝገብ የማህበረሰቡን ማንነት፣ ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋና ሌሎች እሴቶችን አልምቶ ለመጠቀም እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የአድዋን ድል ለመዘከር በማሰብ በጥቂት ባለ ራዕይ አባቶች የተመሰረተው የአገው ፈረሰኞች ማህበር በ83 ዓመታት ጉዞው አባላቱን ከ62 ሺህ በላይ ማድረሱንና የፈረሰኞች ፌስቲቫልም በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ይሄን አንጋፋ የአገው ባህል፣ እሴትና ሁለንተናዊ መስተጋብር መገለጫ የሆነውን በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ለማሳለጥ ማህበሩ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የማህበሩን እሴት በማጥናትና በመሰነድ ምስክር ወረቀት እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ዩኒቨርሲቲው ያቋቋመው የአገው ጥናት ተቋም ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል።

ተቋሙ በፈረስ የሚታጀቡ በዓላትን፣ ሁነቶችን፣ ስለ ፈረስና ማህበሩ የተነገሩ ስነ ቃሎችን እንዲሁም የእደ ጥበብ ውጤቶችንና እውቀቶችን አጥንቶ በመሰነድ መስፈርቱ ማሟላት በመቻሉ የመጣ ውጤት እንደሆነም አስረድተዋል።

እሴቶቹ ሳይበረዙና ሳይከለሱ ከትውልድ ትውልድ ተላልፈው ዛሬ ላይ መድረሳቸውን የጠቆሙት ዶክተር ጋርዳቸው፣ "በቀጣይ በፈጠራና ጥበብ በማገዝ ለመስህብ ሃብትነት መጠቀም ይገባል" ብለዋል።

የአገው ፈረሰኞች እሴትና ባህል ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን እንደሚወጣ አስረድተዋል።

ዛሬ በተካሄደው የፈረሰኞች የሙዚቃ ፌስቲቫልና የልጃገረዶች የቁንጅና ውድድር ላይ የ12 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የባህል ቡድኖች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም