ቀጥታ፡

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዲጂታል መተግበሪያው እስከ አንድ ሺህ ዶላር መላክ ይችላሉ - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አዲስ አበባ( ኢዜአ) ጥር 22 ቀን 2015 በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሐዋላ አገልግሎት ዲጂታል መተግበሪያው ከአምስት እስከ አንድ ሺህ ዶላር መላክ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።

በጊዜያዊነት ከዘጠኝ አገራት ገንዘብ መላክ እንደሚቻልም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‘ኢትዮ ዳይሬክት‘ (EthioDirect) የተባለ የሐዋላ አገልግሎት መስጫ ዘመናዊ ዲጂታል መተግበሪያ ይፋ አድርጓል።

ባንኩ ከኤግል ላየን ሲስተም ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር በመተባበር መተግበሪያውን ማበልጸጉን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ የባንክ ዘርፉን በማዘመንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአገርን ልማት ማፋጠንና ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬን መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህም አጋዥ የሚሆን ‘ኢትዮ ዳይሬክት‘ የተባለ የሃዋላ አገልግሎት መተግበሪያ ይፋ መደረጉን ጠቁመው በቀጣይ በhttps://www.ethiodirect.com አገልግሎቱ እንደሚቀርብ አመልክተዋል።

የመተግበሪያው ይፋ መሆንም በውጭ አገራት ያሉ ወገኖች ወደ አገር ቤት ፈጣንና አስተማማኝ የሃዋላ አገልገሎት እንዲያገኙና ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሀገር ውስጥና በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ የባንኩ ደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙ መሆኑን ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።

አዲሱን መተግበሪያ መጠቀም ተገልጋዮችን ተጨማሪ ወጪ የማይጠይቅ መሆኑን ገልጸው በጊዜያዊነት ከካናዳ፣ እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ጣልያን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስዊድን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ እንግሊዝ እና ሳዑዲ አረቢያ የውጭ አገር ገንዘብ መላክ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በቀጣይም ባንኩ ከቪዛ ኢንተርናሽናል ጋር በመነጋገር ወደ ሌሎች የዓለም አገራት አገልግሎቱን ለማስፋት ማሰቡን ጠቁመዋል።

በመተግበሪያው ከአምስት እስከ አንድ ሺህ ዶላር መላክ የሚቻል መሆኑን ጠቁመው የተላከውን ገንዘብ መቀበል የሚቻለው ለጊዜው ወደ ተቀባዩ የባንክ አካውንት ሂሳብ በማስገባት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ በሲቢኢ ብር ዋሌት እና በጥሬ ገንዘብ ደንበኞች ከባንኩ ቅርንጫፎች የሚወስዱበት አማራጭ ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት አቶ አቤ።

በ1935 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁን ላይ ከ1 ሺህ 800 በላይ ቅርንጫፎች እንዲሁም ከ34 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም