ባህላዊ የስፖርት አይነቶችና ፌስቲቫሎች ይዘታቸውን እንዳይለቁ ለመጠበቅ የዜጎች ድርሻ ወሳኝ ነው - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

20

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 22 ቀን 2015 ባህላዊ የስፖርት አይነቶችና ፌስቲቫሎች ይዘታቸውን እንዳይለቁ ለማድረግ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ሶስተኛው የሲዳማ ክልል አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በሐዋሳ ዛሬ ተጀምሯል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት "ኢትዮጵያ በውስጧ ያሏት ብዝሃነቶች አስደማሚና ድንቅ የሆኑ የባህላዊ ስፖርቶችና ፌስቲቫሎች ባለቤት እንድትሆን አድርገዋታል" ብለዋል።

ባህላዊ ስፖርቶችና ፌስቲቫሎች በአግባቡ ከተጠኑና ከለሙ ለሕዝቦች ማህበራዊ መስተጋብር ማጠናከሪያነትና ለቱሪዝም አገልግሎት ያላቸው ጠቀሜታ ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፋፊ ባህላዊ ስፖርቶችና ፌስቲቫሎች በማልማት ለሕዝቦች ትስስር፣ ለስፖርታዊ ውድድርና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ማጠናከሪያነት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

የሲዳማ ክልል በባህላዊና በዘመናዊ የስፖርት እንቅስቃሴ ለሀገራዊ የስፖርት ልማት የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የሚያደርገውንም ጥረት አድንቀዋል።

ማህበረሰቡ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ባህላዊ የስፖርት አይነቶችና ፌስቲቫሎች ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ በዘመናዊ መንገድ የማልማት ስራ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል።

የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍሬው አሬራ በበኩላቸው የውድድሩ ዓላማ በቀጣይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው ባህላዊ የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መመልመል ነው ብለዋል።

ክልሉ በባህላዊ ስፖርቶችና ፌስቲቫሎች ውድድር በመሳተፍ ባህሉን በማስተዋወቅና የስፖርት ዘርፉን በማጠናከር ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልል ለሶስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የባህል ስፖርትና ፌስቲቫል ውድድር ለአስር ቀናት ይቆያል።

በውድድር እና ፌስቲቫሉ ከአንድ ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን ገና፣ቀስት፣ ኩርቦ፣ ትግል፣ ቡብ፣ ሻህ፣ ገበጣ ጨምሮ የባህል ትርኢቶችን መካተታቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም