የብዝሃ ሕይወት ዝርያዎች አይነት መመናመን የፖሊሲ አውጪዎች ትኩረትን የሚሻ ነው -የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የብዝሃ ሕይወት ዝርያዎች አይነት መመናመን የፖሊሲ አውጪዎች ትኩረትን የሚሻ ነው -የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ( ኢዜአ) ጥር 22 ቀን 2015 ፖሊሲዎች ሲወጡ በብዝሃ ሕይወት የዝርያ አይነቶች እየታየ ያለውን መመናመን ምላሽ መስጠትን ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳሬክተር ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ሃብት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሆነና በተለይም ስንዴ፣ ማሽላና ጤፍ የመሳሰሉት የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የግብርና ብዝሃ ሕይወት ዝርያዎች ቀደም ሲል የነበራቸው የዝርያ ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መጥቷል ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ምክንያት በሚከሰት ድርቅ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የእንስሳት ብዝሃ ሕይወት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በእጽዋት ብዝሃ ሕይወት ወይራ፣ ዝግባና ቀረሮ የተሰኙ አገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች ላይም ለመመናመን አደጋ መጋለጣቸውን እንዲሁ።
በኢትዮጵያ የግብርና፣ እንስሳትና እጽዋት ብዝሃ ህይወት ላይ እየተከሰቱ ያሉ የዝርያ መመናመንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የሚወጡ ፖሊሰና ሕጎች ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ነው ዶክተር ፈለቀ የገለጹት።
ለዚህም ኢንስቲትዩቱ የሚሰራቸው ጥናትና ምርምሮች ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውሉ ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ ለብዝሃ ሕይወት ሀብት መመናመን መሰረታዊ ምክንያቶችን በመለየት ቀጣይ መሰራት ያለባቸውን ተግባራት ያመላከተ ብሔራዊ የሥርዓተ-ምህዳር ዳሰሳ ጥናት አድርጎ በመጽሃፍ መልክ አቅርቧል።
የዳሰሳ ጥናቱን ለፖሊሲ ግብዓትነት መጠቀም እንደሚቻል ነው ዶክተር ፈለቀ ያመለከቱት።
በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የአገር በቀል እጽዋት ላይ ትኩረት ማደረጉ ስርዓተ-ምህዳርን ለማስቀጠል አስተዋጽኦ እንዲሚያደርግም ጠቁመዋል።
የብዝሃ ህይወት ሃብት እጽዋትን፣ እንስሳትና ደቂቅ አካላትን የሚያካትት የስርአተ-ምህዳር አካል ነው።