የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ የብርሃን ምንጭና የምግብ ማብሰያ ከመሆን ባለፈ የደን ውድመትን አስቀርቶልናል- አርሶ አደሮች

26

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2015 የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ የብርሃን ምንጭና የምግብ ማብሰያ ከመሆን ባለፈ የደን ውድመትን አስቀርቶልናል ሲሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሲዳማ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች በአማራጭ የኢነርጂ ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱም በሲዳማ ክልል ውጤታማ በመሆን ላይ የሚገኘው የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ማስፋት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

አርሶ አደር ብዙነሽ ሶያ እና አለማየሁ ለማ በሲዳማ ክልል ወንዶ ገነት ወረዳ ወሻና ሶየማ መንደር ሁለት ቡና መስክ በሚባለው አከባቢ ነዋሪዎች ናቸው፡፡

የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን መጠቀም ከጀመሩ ከአራት ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ ገልጸው ከማገዶ ተጠቃሚነት ገላግሏቸው በጭስ ምክንያት ይደርስባቸው ለነበረው የጤና ችግርም መፍትሄ እንደሆናቸው ተናግረዋል።

የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ በአካባቢው ይደርስ የነበረውን የደን ውድመት በማስቀረት የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ የብርሃን ምንጭ፣ የምግብ ማብሰያና ለሌሎችም ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ጠቅሞናል ብለዋል።

በቴክኖሎጂው የሚገኘው ተረፈ ምርትን ወደ ኮምፖስትነት በመቀየር ለተለያዩ የጋራ አትክልቶችን በማምረት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ ሌላኛው አርሶ አደር አለማየሁ ለማ፤ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ የምግብ ማብሰያና ብርሃን ከመሆኑ ባለፈ በቴክኖሎጂው የሚገኘውን ተረፈ ምርት ወደ ኮምፖስትነት በመቀየር የጓሮ አትክልት እያለሙበት መሆኑን ይናገራሉ።

የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ለንጹህ አካባቢ የሚመረጥ፣ ለአጠቃቀም ምቹ፣ ጊዜ ቆጣቢና የጤና ችግር የማያስከትል በመሆኑ በብዙ መልኩ ጠቅሞናል ሲሉ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ማአድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ሃላፊ መስፍን መጪካ፤ በክልሉ ከዚህ ቀደም የ12 ወረዳ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደነበሩ ገልጸው አሁን ላይ በሰባት ተጨማሪ ወረዳዎች ላይ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ እስካሁን ከ1ሺ 850 በላይ አባ ወራና እማወራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡:

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አወቀ አምዛዬ፤ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ የአርሶ አደሩን ህይወት እየቀየረ መሆኑን በጉብኝቱ ተመልክተናል ብለዋል።

በመሆኑም የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን በሌሎች አካባቢዎችም በስፋት ጥቅም ላይ መዋል አለበት ብለዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ባዮጋዝ ፕሮግራም ማናጀር ተመስገን ተፈራ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ከ165 ሺህ በላይ አባወራዎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሲዳማ ክልል ሌሎች ከሃይል አማራጭ ጋር የተገናኙ ፕሮጀክቶችንም ጎብኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም