ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለች- በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር

29

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 22/2015 ሩሲያ እንደትላንቱ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ገለፁ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸው በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን አዎንታዊ ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ማንሳታቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም ጊዜ አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ኢትዮጵያ ለግጭት አፈታት ተግባራዊነት እየሠራች መሆኑን ጠቅሰው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ በሠላም የተቋጨው ግጭት የዚህ ተግባራዊነት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ድምፅ የማይሰማበትና ዘላቂ ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ እንዲተከል ሰፋፊ ስራዎች እየተከወኑ መሆኑን አፈ-ጉባኤው ለአምባሳደሩ አብራርተውላቸዋል፡፡

አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው ሩሲያ እንደትናንቱ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በሩሲያ የላይኛው ምክር ቤት (የፌዴሬሸን ምክር ቤት) መካከል ያለው መልካም ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገር እንዳለበትም በውይይታቸው ወቅት ተጠቁሟል፡፡

ለትብብሩ መጠንከር ይረዳ ዘንድ በቅርቡ በሞስኮ በሚካሄደው የሩሲያና አፍሪካ ምክር ቤቶች ጉባዔ ላይ አፈ-ጉባኤ አገኘሁ እንዲሳተፉ ከሩሲያ ፌዴሬሽን የተላከውን የጥሪ ደብዳቤ ማስረከባቸውን ከፌዴሬሽን ምክር -ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም