የዓድዋ-ራማ የ40 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ፕሮጀክት በተያዘለት መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ-ራማ የ40 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ፕሮጀክት በተያዘለት መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው
አክሱም መስከረም 24/2011 የዓድዋ-ራማ የ40 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት በተያዘለት መርሃ ግብር እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ። ፕሮጀክቱ የፌደራል መንግሥት በመደበው 807 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተሰራ ነው። መንገዱ ለኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነም ተገልጿል። የባለሥልጣኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን መንድሙ ለኢዜአ እንደስታወቁት፣ግንባታው በታህሳስ 2010 የተጀመረው ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ መርሃ ግብር እየተገነባ ነው ብለዋል። ግንባታው በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ደረጃውን እንዲያድግ መደረጉን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የራማ ከተማን ጨምሮ በመሥመሩ ለሚገኙ የትግራይ ክልል ከተሞች እድገትና ለኢትዮ-ኤርትራ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በዚህም የአገሮቹን የንግድ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰውና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክረውም አስረድተዋል። በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኜ አረጋ የፕሮጀክቱ ግንባታ አሁን 20 በመቶ መድረሱንና የአፈር ቆረጣ፣ሙሌትና የቱቦዎች ቀበራ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። ሥራው አስቸጋሪ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ ባለው አካባቢ የሚከናወን ቢሆንም፤ ደረጃውን ጠብቆና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ለ400 ሠራተኞች ሥራ መፍጠሩንም ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። የራማ ከተማ ነዋሪ አቶ ሃፍታይ ገብሩ እንዳሉት፣መንገዱ ለአደጋ ተጋላጭ እንደነበር አውስተው፤ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመፍጠርና ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ መፋጠን የጎላ ድርሻ እንደሚያበረክት ተናግረዋል። መንገዱ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስና ለራማ ከተማ ዕድገትና ባለሃብቶች የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማሳደግ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ። ሌላኛው የከተማ ነዋሪ አቶ ዓንዳይ አብርሃ፣ የመንገዱ ግንባታ ወደ አድዋ ከተማ ለመጓዝ ያጋጥማቸው የነበረውን ችግር እንደሚያቃልለው ገልጸዋል።የትራፊክ አደጋ ለመቀነስም ይረዳል ብዬ አምናለሁ ብለዋል።