ቀጥታ፡

በኳታር የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት መስኮች የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 21/2015 በኳታር የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት መስኮች የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አሊዪ ተናገሩ።

አምባሳደር ፈይሰል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ በኳታር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው። 

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው የልማት መስኮች ማሳተፍ ትኩረት የተሰጠው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው ይህንንም ገቢራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

ይህንንም ተከትሎ ዳያስፖራው በተለያዩ መስኮች ላይ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በተለይም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።  

ዳያስፖራው ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ በፋይናንስ በሌሎችም ዘርፎች የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።  

ከ25 አገራት የተውጣጡና በአገራቸው ጉዳይ የላቀ ተሳትፎ የነበራቸው 52 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች በቅርቡ እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን የታላቁ ህዳሴ ግድብንም ጎብኝተዋል። 

እንደ አምባሳደር ፈይሰል ገለጻ፤ ዳያስፖራው የታላቁ ህዳሴ ግድብን መጎብኘቱ በግድቡ ግንባታ ሲያደርግ የነበረው ድጋፍ ፍሬውን ለማየት እድል የሰጠና ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋ እንዲያጠናክር የሚያግዘው ነው።  

በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በተፈጠረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዳያስፖራው አበረታች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል። 

በዚህ ረገድ በኳታር የሚገኘው ዳያስፖራ ለተፈናቃይ ወጎኖች የሚያስፈልጉ ድጋፎችን በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት።   

በሌላ በኩል በኢትዮጵያና በኳታር መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ኳታር ከኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም፣ ቡናና ሌሎች የእንስሳት ውጤቶችን ከኢትዮጵያ የምትወስድ ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ኬሚካሎችን ከኳታር ታስገባለች።  

ኢትዮጵያ ወደ ኳታር የምትልካቸው ምርቶች እሴት የተጨመረባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ የገለጹት አምባሳደር ፈይሰል በዚህ ረገድ የበለጠ መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።  

ለዚህም ደግሞ ኢትዮጵያ በንግድ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም የኳታር ባለኃብቶች እንዲያውቁት ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው ያብራሩት። 

በተያዘው ዓመት የኳታር አስጎብኚ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎብኙ መታቀዱን ገልጸው ይህም ኳታር ኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻ እንድታደርግ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም