ቀጥታ፡

የከባድ ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎችን ዕውቀትና ክህሎት ለማጎልበት ስልጠና እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 24/2011 የኢትዮጵያ አገር አቋራጭ ከባድ ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎችን ዕውቀትና ክህሎት ለማጎልበት ስልጠና እየተሰጠ ነው። ከዚህ ቀደም ከማሰልጠኛ ተቋማትና አሽከርካሪ ባለሙያዎች ተውጣጥተው ስልጠና ያገኙ ባለሙያዎች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። ዕውቅና የተሰጣቸው ባለሙያዎች እንደገለጹት፤ በስልጠናው የሰው ህይወትና ንብረት ደህንነቱን በመጠበቅ ለማሽከርከር የሚያስችል ወቅቱ የሚጠይቀውን የእውቀትና ክህሎት አግኝተዋል። የትራንስፖርት ባለሥልጣንና የዓለም የምግብ ፕሮግራም በመተባበር ለሁለት ቀን የሚሰጠው የንድፈ-ሀሳብና የተግባር ስልጠና የአገር አቋራጭ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ወቅቱ የሚጠይቀውን ዕውቀት በማግኘት የህይወትና የንብረት ደህንነትን ለመጠበቅ የሚያግዛቸው እንደሚሆን ተናግረዋል። የተሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ አሽከርካሪ ባለሙያዎች፣ ትራንስፖርት ኩባንያዎችና ማህበሮች የሚሳተፉበትን ይህንን ስልጠና የሚሰጡት በዘርፉ ዓለም ዓቀፍ ልምድና እውቀት ያላቸው ከእንግሊዝ፣ ኬንያና ታንዛኒያ በመጡ ባለሙያዎች እንደሆነ ታውቋል። የትራንስፖርት ባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳሬክተር ወይዘሮ አልማዝ በየኖ እንደገለጹት፤ ስልጠናው የሚካሄደው የአሽከርካሪውን ሁለንተናዊ ክህሎትና ዕውቀት ለማሳደግ ታልሞ ነው። በዚህም ስለ መንገድ መፍረስና ውጤቶቻቸው፣ የትራፊክ ግጭቶች፣ የሞት አደጋዎችና ጉዳቶች በተመለከተ ማብራሪያም ይሰጥበታል። የአሽከርካሪ ሥልጠናው የአሽከርካሪውን የእውቀት፣ የመንገድ ደህንነትና ደህንነቱን የጠበቀ ማሽከርከርን በተመለከተ ክህሎትን ለማሻሻል ያለመ ነው። በተጨማሪም በዘርፉ ሥራ አመራር፣ ግዥ፣ ጥገናና ፋይናንስ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል። እንደወይዘሮ አልማዝ ገለጻ፤ ከኢትዮጵያ - ጂቡቲ ባለው መንገድ የወጪና የገቢ ምርት በበርካታ ተሽከርካሪዎች ተጓጉዞ የሚመጣ ነው። በመስመሩ ላይ የትራፊክ መጨናነቅና መጉላላት እንዳይኖር ለመከላከል ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ የመቀመር ስራ እየተሰራ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በዛሬው ዕለት የአሰልጣኞች ሥልጠና የእውቅና ወረቀት ከተሰጣቸው መካከል ከ20 ዓመት በላይ የአሽከርካሪነት ልምድ ያላቸው አቶ ጉደታ ዳዲ እንደሚሉት፤ ቀደም ብሎ የወሰዱት ስልጠና ብቁ አሰልጣኝ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ሰዎች መኪና በሚያሽከረክሩበት ወቅት ትኩረታቸውን የሚያሳጡ ተግባራትን ማስወገድ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። በተለይም እንደ ተንቀሳቃሽ ስልክና ሌሎች አእምሮአቸውን የሚሰርቁ ተግባራት ማከናወን በቅጽበት ለከፋ አደጋ የሚያጋልጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ አቶ ጉደታ ገልጸዋል። በአገሪቷ የሰው ህይወትን በመቅጠፍ ከተፈጥራዊ በሽታዎች ይልቅ የተሽከርካሪ አደጋ ገዳይ እየሆነ መምጣቱን የሚያስታውሱት የስልጠናው ተሳታፊ አቶ ምትኩ ሁንዴ፤ አንድ የአገር አቋራጭ አሽከርካሪ ማግኘት ያለበትን ዓለም ዓቀፍ የእውቀትና ክህሎት ከስልጠናው ማግኘታቸውን አስረድተዋል። አቶ ምትኩ በሚሰሩበት ኩባንያ ውስጥ ለሚገኙ ከ400 በላይ አሽከርካሪዎች ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት እንደሚያካፍሉ ጠቁመዋል። ወደፊት የሚሰጠውን ዓለም ዓቀፋዊ ስልጠና በመውሰድ የምስክር ወረቀት ያልያዘ የተሽከርካሪ አሽከርካሪ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ውጭ ወደ ተለያዩ አገሮች ድንበር አቋርጠው ማለፍ እንደማይችል ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም