ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች አቅራቢዎች በካርቱም ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ

ጥር 21/2015(ኢዜአ)የኢትዮጵያ የተለያዩ የወጪ ምርቶች አቅራቢና አምራች ኢንተርፕራይዞች ከጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ተከታታይ ቀናት በካርቱም እየተካሄደ ባለው 40ኛው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኝ ተገለጸ።

በንግድ ትርኢቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት በሱዳን የኢፌዴሪ ምክትል የሚሲዮን መሪ አቶ መኮንን ጎሳዬ፣ የሱዳን የንግድና አቅርቦት ሚኒስትር አማል ሳላህ ሰኢድ መሃመድና የካርቱም ግዛት አስተዳዳሪ አህመድ ኦትማን ሃምዛ እና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ አምራች ኢንተርፕራይዞች ያቀረቧቸውን ልዩ ልዩ ምርቶች መመልከታቸውም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የቡና አፈላል ሥነ ስርዓት ላይም ባለስልጣናቱ መታደማቸው ተመላክቷል።

በንግድ ትርኢቱ ላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የቱርክ፣ የአልጄሪያ፣ የኬንያ፣ የዩጋንዳ እና የሱዳን ኩባንያዎች ተሳትፎ በማድረግ እንደሚገኙ በሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ መረጃ ያመላክታል።

የንግድ ትርኢቱ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስርና የንግድ ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ ከፍተኛ ጠቃሜታ እንደሚኖረው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም