ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ለቀጠናው አገራት የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው

ሀዋሳ መስከረም 24/2011 የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ለቀጠናው ሃገራት መልካም ተሞክሮ እንደሚሆን ለ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ተጋብዘው የመጡ የውጭ ሃገራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና አምባሳደሮች ገለጹ። ተጋባዦቹ ዛሬ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመገኘት የታይዋኑን ኤቨረስት ኩባንያና የቻይናውን ጂፒ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ  የስራውን እንቅስቃሴ ተመልክተዋል። የሩዋንዳው አር.ፒ.ኤፍ ፓርቲ ተወካይ ሚስተር ቲቶር ተርሜና በጉብኝቱ ላይ ለኢዜአ እንደገለፁት ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለቀጠናው የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጻ የሚያበረክት ነው። ምርቱን ለውጭ አገራት በመላክ ምንዛሪ የሚያስገኝ በመሆኑ የኢንዳስትሪ እድገት እንደ አዲስ ለሚጀምሩ የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት ሊሆን እንዲሚችል መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ "ፓርኩ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንና በአህጉር ደረጃ ያለውን የገበያ ክፍተት ለመሸፈን እየሰራ መሆኑን ተገንዝብያለሁ" ብለዋል። ፓርኩ ዘመናዊ መሆኑን የተናገሩት ሚስተር ቲቶር "ኢትዮጵያ በትክክለኛ ኢንዳስትሪ ልማት መስመር ላይ ናት" ብለዋል። የጀርመኑ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ ኮንስታንቲን ግሩንድ በበኩላቸው በፓርኩ የአምራች ኢንስትሪዎች እንቅሰቃሴ መደነቃቸውን ገለፀዋል። ኢትዮጵያ ለማሳካት ከያዘችው የኢንዳስትሪ ልማት እቅድ አንፃር በዘርፉ እያደረገች ያለው ሽግግር በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ከጉብኝታቸው መገንዘባቸውን ተናግረዋል። "በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የሃዋሳ ኢንዳስትሪ ፓርክ ሞዴል እንደሚሆን እምነቴ ነው" ብለዋል፡፡ "በፓርኩ የስራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር ትልቅ ስራ ተሰርቷል" ያሉት ኮንስታንቲን ግሩንድ ፓርቲያቸው በቀጣይ ከኢሀዴግ ጋር የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚያጠናክር አመላክተዋል። "በፓርኩ በተመለከትኳቸው አምራች ኩባንያዎች በስራው እንቅስቃሴ ተደንቄያለሁ" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ታን ጂያን ናቸው። ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ጠንካራ ግንኙነት ፓርኩ በቻይና ኩባንያ መገንባቱን ያስታወሱት አምባሳደሩ ለሀገራቱ ግንኙነትና ትብብር  ጥሩ ምሳሌ መሆኑን ተናግረዋል። በፓርኩ ያደጉና በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት አምራች ኩባንያዎች መኖራቸው ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ጥሩ መድረክ ፈጥሯል" ያሉት ሚስተር ታን ጂያን " ፓርኩ ዘመናዊና በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን መገንዘባቸውንም ገልፀዋል። አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስን ወክለው የተገኙት በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢኩበል ጃዝብሃይ በበኩላቸው"ፓርኩ በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ልማት በማደግ ላይ መሆኑን ያሳያል" ብለዋል። ከዚህ በፊት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የኢሀዴግ ጉባኤ በተሳተፉበት ወቅት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የኢንዱስትሪ ዞን መጎብኘታቸውን ያስታወሱት አምባደሩ አሁን ላይ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት እድገትና መሻሻል ማሳየቱን መገንዘባቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም