ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወደፊት ሊያሻግር የሚችለው አንድነትና የጋራ ጥረታችን ብቻ ነው - የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ

ሐዋሳ (ኢዜአ) ጥር 20/2015 "ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወደፊት ሊያሻግር የሚችለው አንድነትና የጋራ ጥረታችን ብቻ ነው" ሲሉ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

"የሕብረተሰባችን ተሳትፎ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለብልጽግና ጉዟችን ስኬት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ውይይት በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ እንዳሉት ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች የሚገኙባት ሀገር ናት፤እነዚህ ማንነቶች በሕብረ ብሔራዊ አንድነት መንፈስ የበለጠ እንዲያስተሳስሩን በማድረግ ለሀገር ልማት ማዋል ይገባል።

“ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ወደፊት ሊያሻግር የሚችለው አንድነትና የጋራ ጥረታችን እንጂ መለያየታችን ባለመሆኑ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን በማጠናከር ለሀገር ልማት በጋራ መነሳት ይገባናል” ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ''ከሕዝብና ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ አካላት ሀገራችንን ለማፍረስ በቋንቋ፣ ብሔርና ሀይማኖት ህዝቦቿን ለመበታተን የሚያደርጉትን ሩጫ ለማስቆም አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል'' ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ አንድ ሆነው የሀገራቸውን ሰላም ሲያስጠብቁ እንደነበሩት ሁሉ አሁንም በመመካከርና በመወያየት አንድ ሆነው በመቆም ለሀገር ልማት የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከሀዋሳ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም