ቀጥታ፡

ሀገራዊ ችግሮች እንዴት ማለፍ እንዳለብን ከሕዝብ ጋር መወያየት ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል

ጅማ (ኢዜአ) ጥር 20/ 2015 ሀገራዊ ችግሮች እንዴት ማለፍ እንዳለብን ከሕዝብ ጋር መወያየት ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ነው" ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

በጅማ ከተማ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ መንግስታት የሥራ ኃላፊዎች በሀገራዊ የሰላምና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሕብረተሰቡ ጋር ተወያይተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ "ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ፈተናዎች ያለፈች ቢሆንም አሁን ያልተሻገራቻቸው ፈተናዎች ከፊቷ አሉ" ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን እንዴት አድርገን የተሟላና አስተማማኝ ሰላም እንዲሁም የተጀመሩ የልማት ጉዟችንን እንዴት እናስቀጥል? በሚሉ ሀሳቦች ላይ ከሕብረተሰቡ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ፈተናዎች በጥንቃቄ እና ብልሃት ለማለፍ ሕብረተሰብን ያማከለ መፍትሔ ማበጀት ቁልፍ መሆኑን አመልክተዋል።

በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገጠሟት ያሉ ችግሮችን ከሕብረተሰቡ ጋር በመመካከር ለመፍታትና ሰላማዊ ሀገር ለማስቀጠል የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ገበያ በጥላቻ፣ በጥርጣሬና በመከፋፈል የተሞላ እንዲሆን የተሰራን ስህተት አርሞ ለማስተካከል የሁሉም ሕብረተሰብ ድርሻ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ዜጎች ገንቢ ሀሳብ በመስጠት ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የድርሻውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ እንዳመለከቱት፤ "ምሬት በወለደው የሕዝብ አመፅ በመጣ ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን አስተናግዳለች፡፡"

የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ዝርፊያና ብዝበዛ የበዛበት፤ ስራ አጥነት የተንሰራፋበት፤ የብድር ጫና ያየለበት እንዲሁም በውስጥ የነበሩ ፓርቲዎች የእኩል ተሳትፎ ጥያቄ የነበረበት በመሆኑ ለውጡን ወደ ፊት ገፍቶታል ብለዋል።

"ለውጡ በተለይ ምን አሳካን?፣ ምን ገጠመን? እና ምን ተማርን? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ችግርን ተቋቁሞ ማልማትን ፈተናዎችን በብልሃት ማለፍን እንዲሁም በአንድነት በመጋፈጥ ረገድ ልምድ ያገኘንበት ነበር" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣በጅማ ከተማ የሚኖሩ ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም