ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚሻው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ

85

ሰለሞን ተሰራ

(ኢዜአ)

ዲጂታል ኢኮኖሚ በዋናነት በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እገዛ የሚገነባ ኢኮኖሚ ሲሆን በኢንፎርሜሽን እና ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) የታገዙ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን፣ ስርዓቶችን፣ ግብይቶችን እና ግንኙነቶችን ያጠቃልላል፡፡

በዚህም ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው ስራዎቻቸውን መከወን ከመቻላቸውም ባለፈ የንግድ ስራ ዕድሎችን በማስፋት በኩል ጉልህ አበርክቶ አለው። የምርትና አገልግሎቶች ግዢና ስርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጥታ እንዲስፋፋ በማድረግ በኩልም የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ሚናው የጎላ ነው።

ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችልና የአገልግሎቶችን ጥራት ለማሻሻል እና ለኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ ነው። የወረቀት ገንዘብን በሂደት ለማስቀረት የሚያስችልና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያግዝ በመሆኑ ሌብነትን በመቀነስ በኩልም ፋይዳው ጉልህ እንደሆነም ይገለጻል።

በተለይ ያደጉ አገራት ከዲጂታል ኢኮኖሚ ትሩፋቶች መቋደስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። እየተፈጠሩ ያሉ ምቹ ሁኔታዎች በዲጂታል መንገድ የሚፈጸም የገንዘብ ዝውውር እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ምጣኔ ሀብቱ 11 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር ያስመዘገበ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ ምርት 15 ነጥብ 5 በመቶውን እንደሚይዝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ በዓለም ዙሪያ ልዩ ትኩረት እየተቸረው የሚገኝ ሲሆን በአፍሪካም መንግስታት ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ በማሰብ ፈጣንና ስር ነቀል የዲጂታል ስትራቴጂ አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም የክፍያ ስርዓቶችን ወደ ዲጂታል በማሳደግ አበረታች ውጤት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡

በተለይ የቴሌኮም ዘርፉን ለግል ባለሃብቶች ክፍት በማድረግ በዘርፉ የፈጠራና የውድድር መንፈስ እንዲዳብር በር መክፈቷ በዘርፉ ትልቅ ውጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል፡፡ የባንክ አገልግሎትን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የተጀመረው ጉዞም ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ይታመናል።

ነገር ግን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጠንካራ የመረጃ እና የግንኙነት መሰረተ ልማት አውታሮችን መዘርጋት የሚሻ በመሆኑ ጉዞው በፈተና የተሞላ መሆኑ አይቀሬ ነው። በዘርፉ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመምጠቅና የልማት ራዕይን እውን ለማድረግ በዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የግድ እንደሚል የዘርፉ ምሁራን የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡

ለዚህ ይረዳ ዘንድ ባለሃብቶችን የሚያማልሉ ማበረታቻዎችን በማስቀመጥ በዕድሉ መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ማደግ ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ላላቸው ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦትን በማሟላት ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ጋር እንዲሰሩ በማስተሳሰር ዘርፉን ማሳደግ ያሻል፡፡

ለዲጂታል ኢኮኖሚው መሰረት መጣል

ኢትዮጵያ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን በማለም ያወጣችው የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ (ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም) በመታገዝ በዲጂታል ሽግግር ቀዳሚ ግቦች ያለቻቸውን ጉዳዮች በማስቀመጥ ወደ ትግበራ ገብታለች፡፡

የዲጂታል መታወቂያ መተግበር፣ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትና የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ ደግሞ ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ናቸው፡፡

እነዚህን ዘርፎች ግልጽና ወጥ በሆነ ስትራቴጂ ወይም በብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ እና በባንክ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በማስተሳሰር የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመንና ከወረቀት ንክኪ የፀዳ የግብይት ሥርዓት በመፍጠር የፋይናንስ አካታችነትን የያዘ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሰራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በመቅደም የተለያዩ ፖሊሲዎችን አውጥቶ ዘርፉን ለማዘመን መንቀሳቀሱን ብዙዎች በበጎ ጎኑ ያነሱታል፡፡ በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የዲጂታል መታወቂያ አሰጣጥ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሲገኝ የዲጂታል ክፍያ ስርዓቱም ውጤት አስመዝግቧል፡፡

ከዚህ ባለፈ በኤሌክትሮኒክስ ታግዞ የሚከናወነው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና የሳይበር ደህንነት ጥበቃ የራሳቸው የሆነ ሰፊ ስትራቴጂ የሚፈልጉ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የቴሌኮም እና የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር መንግስት በመደበኛ የብሮድባንድና በኢንተርኔት ክፍያ ላይ ቅናሽ በማድረጉ በየዕለቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ ቢገለጽም በኢኮኖሚያዊ ዝውውሮች ላይ ኢንተርኔት የሚጠቀመው የሕብረተሰብ ክፍል ዝቅተኛ መሆኑ እንደ ተግዳሮት ይነሳል፡፡

በኢኮኖሚው ውስጥ ዲጂታላይዜሽን እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመረጃ መረብ ጥቃትና ምንተፋ እየጨመረ መምጣቱም የዘርፉ ስጋት መሆኑ አልቀረም፡፡ ይህንን ስጋት ለመቀነስ ጠንካራና ተዓማኒ የመረጃ መረብ ጥበቃ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት የአይሲቲ ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ፣ የኤሌክትሮኒክስ ንግድን ለማቀላጠፍና ለመቆጣጠር የሚያግዙ አሰራሮችን ለመዘርጋት በትኩረት እየሰራ ይገኛል። መንግሥት የዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን ለሚከተሉ የንግድ ሥራዎች ማበረታቻ በመስጠት ከ200 የበለጡ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶችን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ለመተግበር አቅዶ እየሰራ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አካውንታንቶችና ኦዲተሮች ቦርድ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ስምምነት በማሰር አገልግሎት ፈላጊዎች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በኦንላይን ወይም ቴሌብርን በመጠቀም እንዲከፍሉ ማድረጋቸው ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ገቢዎች ቢሮዎችም የክፍያ ሥርዓታቸውን ከቴሌ ብር ጋር በማስተሳሰር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን እውን አድርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችንና ሌሎች ተቋማትን አሰራር በማዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራውን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡

ነገር ግን በኢትዮጵያ 570 የንግድ ተቋማት በ ‘ኢ-ኮሜርስና በኢ-ሰርቪስ' ምቹ ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር ሥራ ቢጀምሩም እነዚህ ተግባራት በጣም አነስተኛና ይህ ነው የሚባል ገቢ የሚመነጭባቸው አለመሆናቸውን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት አገሪቱ መከተል ለሚገባት የዲጂታል ኢኮኖሚ ትግበራ በርካታ ፖሊሲዎችንና ደንቦችን ቢያዘጋጅም ዘርፉን ወደፊት ለማራመድ ፈጣን የቴክኖሎጂ ግንባታ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድ አስተማማኝና በአነስተኛ ዋጋ የሚቀርብ የኔትወርክ ሽፋንና ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት ግድ ይላል፡፡

ቅንጅታዊ አሰራር ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ

ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ለምታደርገው ሽግግር መንግሥት ከሚያወጣው ከፍተኛ ገንዘብ ባሻገር የግሉ ዘርፍ በመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርገውን እገዛ በእጅጉ ትፈልጋለች፡፡

ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበው የፋይናንስ ድጋፍ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የዘርፉ ባለራዕዮች ንግዳቸውንና የፈጠራ ሥራቸውን ለማሳደግና ዲጂታላይዝ ለማድረግ አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡

አሁን ላይ ባንኮች እያደረጉት ያለው የአሰራርና የፋይናንስ አጠቃቀም ማሻሻያ ተቀማጫቸውን በማሳደግ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያጎለብቱ መንገድ ከፍቷል፡፡ ጥቂት ባንኮች ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት የሚያደርጉ ቢሆንም በርካታ ባንኮች ግን ከፍተኛ አቅም ያላቸውን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች "አትራፊ አይደሉም" በማለት ችላ ማለታቸው ለዘርፉ እድገት መጓተት እንደ ምክንያት ተቀምጧል።

ባንኮች፣ ማይክሮፋይናንስ አቅራቢዎችና የኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በዘረጉት አሰራር በመታገዝ አነስተኛ ተቋማቱ በዲጂታል ዋሌት፣ ሞባይልና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎቶች በመታገዝ የበለጠ የፋይናንስ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ በአይ.ሲ.ቲ. ዘርፍ ለተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበውን የፋይናንስ አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ የውጭ ኢንቨስትመንት የምትስብበት መንገድ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በዲጂታል ዲፕሎማሲ ሲታገዝ ብቻ ነው፡፡

ለዲጂታል መሰረተ-ልማት ግንባታና ሰፊ ለሆነው ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚቀርበው የአገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ፈንድ ውስን መሆኑ ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ እ.አ.አ. በ2021 ዘርፉን ለማሳደግ የተገኘው እገዛ ከ60 ሚሊዮን ዶላር አለመዝለሉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለመተግበር የያዘውን ከፍተኛ ራዕይ ዕውን ለማድረግ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከዓለም ባንክ፣ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና የግል ተቋም ከሆነው ማስተር ካርድ እገዛዎችን አግኝቷል፡፡

ከአንድ አገር ወይም ተቋም ጥገኝነት ለመላቀቅ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ አቅም ካላቸው ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ጋር በመተባበር የአይሲቲ ዘርፉን ለማሳደግ በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡

ከስትራቴጂ ወደ ትግበራ

የኢትዮጵያ መንግሥት ኢኮኖሚውን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ታላቅ ራዕይ ሰንቆና ስትራቴጂ ቀርጾ ወደ ስራ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ በተለይም ለዘርፉ ምቹ ከባቢ ሁኔታ የሚፈጥሩ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ቴክኖሎጂዎችና ንግዶች በፈጠራ የታገዙ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅዱ ላይ እንደተመለከተው የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ዝግጁነትን በማጎልበት ረገድ አንድ ለእናቱ የነበረውን ብሔራዊ ዳታ ማዕከል የማሻሻልና ተጨማሪ ሁለት ዳታ ማዕከሎችን የመገንባት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በዚህም ብሔራዊ የዳታ ማዕከሎች ብዛት ወደ ሶስት በማሳደግ ለዲጂታል መታወቂያ የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ወደ ሥራ አስገብቶ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ ነዋሪዎች ተጠቃሚነትን በልማት ዕቅዱ መጀመሪያ ዓመት ከነበረበት 0 በመቶ ወደ 90 በመቶ የማሳደግ ስራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

በመንግስት ኔትወርክ ውስጥ የሚካተቱ የመንግሥት ተቋማት ሽፋን ወደ 95 በመቶ ለማድረስ ግብ የተጣለ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 85 በመቶው ቢያንስ በሰከንድ አሥር ሜጋ ባይት ኮኔክሽን እንዲኖራቸው በማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን የማቀላጠፍ ውጥን ተሰንቆ እየተሰራ ነው።

የመንግሥት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶችን ወደ 2 ሺህ 500 በማድረስ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶችን ሽፋን ወደ 85 በመቶ የማሳደግ ግዙፍ አገራዊ ዕቅድ እየተተገበረ ይገኛል።

በኢኮኖሚና በዲጂታል ትግበራው ላይ ማሻሻያ መደረጉ አዳዲስ የገበያ ተዋናዮችን ለመፍጠርና የባንኩን ዘርፍ ለማሳደግና ለማዘመን አስችሏል፡፡ ይህም ቢሆን አሁንም አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ኢኮኖሚያቸውን ዲጂታላይዝ በማድረግ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ እንዲችሉ የሚቀርበውን የፋይናንስ አቅርቦት አስተማማኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ይህም ምርታማነታቸውን በማሳደግ ለፈጠራ ስራዎች መጎልበት የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ የኢኮኖሚ ሽግግሩን እንዲመሩ ያስችላቸዋል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ በእጅጉ የተደራጀና የተቀናጀ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘመቻ ማድረግ አለባት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዘመቻ በዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ የሚያፈሱ ስመ-ጥር ኩባንያዎችን ለመሳብና የሚያስፈልጋትን የቴክኒክ ድጋፍ ለማግኘት ያስችላታል፡፡

በመሰረታዊነት የአገርን ኢኮኖሚ ዲጂታላይዝ ሊያደርጉ የሚችሉ ዕቅዶች በሚፈለገው ልክ ውጤታማ መሆን የሚችሉት ግን ለዘርፉ የተመቹ ሰፋፊ መሰረተ-ልማቶችን በመዘርጋት ነው። መሰረተ-ልማቶቹ ደግሞ ከፍተኛ አቅም የሚጠይቁ በመሆኑ በትብብር ነው መሳካት የሚችሉት። የግሉ ዘርፍ በዚህ ረገድ ያለበትን ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት መወጣት ይጠበቅበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም