የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በመጀመሪያ ጉባኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ተፈጻሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

213

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 20 ቀን 2015 የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በመጀመሪያ ጉባኤው የስራ እድል ፈጣራን ጨምሮ ያሳለፋቸውን የተለያዩ ውሳኔዎች ገቢራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ለሁለት ሳምንታት የሚቆየው አገር አቀፍ የወጣቶች ጉባዔ አዲስ አበባን ጨምሮ በ21 ከተሞች ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ጀምሯል።

በአጠቃላይ በጉባኤው ላይ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ጉባኤው የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ በታህሳስ ወር 2015 ዓ.ም በአዳማ ባካሄደው የመጀመሪያው ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች መሰረት በማድረግ እንደሚከናወን ተገልጿል።

አገር አቀፍ የወጣቶች ጉባኤው ከሚካሄድባቸው ከተሞች ውስጥ አንዷ አዲስ አበባ ናት።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንት ፈዲላ ቢያ በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንዳለችው፤ ሊጉ በአዳማ ባካሄደው የመጀመሪያ ጉባኤ "ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያላቸውን ውሳኔዎች" ተላልፈዋል።

በጉባኤው በዋናነት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የወጣቶች የስራ እድል መሆኑን ገልጻለች።

የስራ እድል ፈጠራን ጨምሮ ወጣቶች ዘላቂ ልማት፣ ሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የወጣቶችን ተሳትፎ የማጠናከር ሥራ በቀጣይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራበት አመልክታለች።

የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወጣት አንሙት አበጀ፤ ጉባኤው የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የመጀመሪያው የትኩረት ጉዳይ መሆኑን ገልጿል።

ለዚህም በቀጣይ በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሔና ምላሽ ይሰጥበታል ብሏል።

በቀጣይ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ ስራዎች እና ግብርናን ጨምሮ በሌሎች መስኮች በስፋት ለማሳተፍ መታሰቡን አመልክቷል።

አገር አቀፍ የወጣቶች ጉባዔ ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በጉባኤው ላይ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አመራሮች፣አባላት እና ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ የመጀመሪያ ጉባኤውን ከታህሳስ 21 እስከ 26 ቀን 2015 ዓ.ም በአዳማ ማካሄዱ የሚታወስ ነው።

የወጣቶች ሊጉ በጉባኤው የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ጠንካራ የአሰራር መዋቅር መዘርጋት፣ አካታችነት፣ ዘላቂ የሰላም ግንባታና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም