በየዓመቱ የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል የቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቃ ነው

365

ባህርዳር(ኢዜአ) ጥር 20 ቀን 2015 በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በየዓመቱ የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል ጎብኝዎችን እየሳበ የቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቃ መሆኑን የአስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

83ኛውን የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል በልዩ ድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁም መምሪያው ገልጿል።

በዓሉ ከዛሬ ጀምሮ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በቅኔ ምወድስ፣ በጃኖ ባህላዊ አለባበስና በፋሽን ትርኢት፣ በሩጫ ውድድር፣ በሙዚቃ ፌስቲቫል፣ በቁንጅና ውድድርና በጎዳና ላይ የፈረስ ትርኢት እስከ በዓሉ ዋዜማ በድምቀት እንደሚከበር የመምሪያው ኃላፊ አቶ ለይኩን ሲሳይ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ጥር 23/2015 ዓ.ም በዓሉ በባህላዊ ምግብ ዝግጅትና ጉብኝት፣ የፈረሰኞች አይሞሎ፣ በፈረስ ሸርጥና ፈረስ ጉግስ፣ በሽምጥ ግልቢያና ስግሪያ ውድድሮች በድምቀት ተከብሮ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ጎብኝዎችን ቀልብ እየሳበ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ዘርፉን እያነቃቃ መምጣቱን አስታውቀዋል።

በተለይ በዓሉን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓሉ በቅርስነት ተመዝግቦ ከብሄራዊ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የምስክር ወረቀት ቀደም ብሎ እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲም የሙያና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ግንባር ቀደም ሆኖ በጥናቱ እየተሳተፈ መሆኑን አውስተዋል።

በተለይ በዓሉ በድምቀት መከበር ከጀመረበት ከዛሬ ስድስት ዓመት ወዲህ የእንጅባራ ከተማ የጎብኚዎች ቀልብ በመሳብ ኢኮኖሚዋ እየተነቃቃ እንዲመጣ ማገዙን አቶ ለይኩን አመልክተዋል።

የአገው ፈረሰኞች ማህበር ሊቀመንበር አለቃ ጥላዬ አየነው በበኩላቸው፤ በጣሊያን ወረራ ወቅት በፈረስ ተዋግተው ድል ያደረጉና የተሰው ጀግኖች አርበኞችን ለመዘከር ማህበሩ በ1932 ዓ.ም እንደተመሰረተ አስታውሰዋል።

በወቅቱ ከ30 በማይበልጡ አባላት ማህበሩ እንደተመሰረተ ጠቅሰው፤ በተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረትም አሁን ላይ የአባላቱን ቁጥር 62 ሺህ 221 ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።

በቀጣይም በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲሳካ የአባላቱን ቁጥር ወደ 150 ሺህ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እኛም አባቶቻችን ያስረከቡንን ባህል በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቅ ባለፈ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ በማድረግ ሀገራችንንና አካባቢያችንን ለመጥቀም ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በእንጅባራ ከተማ በሚከበረው ዓመታዊ የፈረሰኞች ማህበር በዓል የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም