በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ90 ቀናት ውስጥ ለመፈፀም የታቀዱ ስራዎች በአስደናቂ ፍጥነት እየተከናወኑ ነው--ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ጥር 20/2015 (ኢዜአ)፦ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በ90 ቀን ውስጥ ለመፈፀም የታቀዱ ስራዎች በአስደናቂ ፍጥነትና ጥራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ማህበረሰብ የምንገነባቸው 240 ቤቶችን የያዙ ባለ 5 ወለል 6 ህንፃዎች፣ የአካባቢ ውበት አረንጓዴ ስፍራዎች ማራኪና አካባቢውን መለወጥ በሚያስችል ሁኔታ እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የሌማት ትሩፋት፣ የዳቦና የምገባ ግንባታዎችም በመጠናቀቅ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ብልሽትና ሌብነትን ለመዋጋት መሰረታዊ የቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሰራርን በመጠቀም ለማገልገል ዝግጅት ተደርጎ የተጠናቀቀው አዲሱ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጽህፈት ቤት ህንፃ የቃጠሎ አደጋ ቢያጋጥመውም በከፍተኛ ትኩረትና እልህ በአጭር ቀን ውስጥ መልሶ በተሻለ ሁኔታ ለመስራት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

“በዚህ አጋጣሚ የህብረተሰቡም ሆነ የመንግስት ምንም አይነት ዶክመንት ለእሳት አለመዳረጉን ለማረጋገጥ ችለናል” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም