የኖርዲክ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት አላቸው- አምባሳደር ምሕረተአብ ሙሉጌታ

153

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 20 ቀን 2015 የኖርዲክ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት ማሳየታቸውን በኖርዲክ ሀገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ምሕረተአብ ሙሉጌታ ገለጹ።

በኖርዲክ ሀገራት የኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፊንላንድና ዴንማርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ምሕረተአብ ሙሉጌታ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተመለከተ ኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም ሀገራቱ ለረዥም ዘመናት ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትብብር በማድረግ የሚታወቁ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስክም ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሰሜኑን ክፍል ግጭት ተከትሎ ሀገራቱ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የነበራቸውን ተሳትፎ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይተው እንደነበር አስታውሰው፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ግን በብዙ መልኩ ትብብራቸውን የማጠናከር ፍላጎት ማሳየታቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ሀገራቱ በተለይም የኢኮኖሚና የልማት ትብብራቸውን በላቀ መልኩ የማስቀጠል ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያን ችግር በሰላማዊ ውይይት በመፍታት ሂደት የመንግሥትን ቁርጠኝነት ማድነቃቸውን አስታውሰው፤ ለስኬታማነቱ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት አላቸው።

በቀጣይ በተለይም በሀገሪቷ የመልሶ ግንባታ ላይ ለመተባበር ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን አምባሳደር ምሕረተአብ ገልጸዋል።

የኖርዲክ ሀገራት ኖርዌይን ጨምሮ በኢትዮጵያ የትምህርት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የዘላቂ ልማትና ሌሎችንም የልማት ክንውኖች በመደገፍ ይታወቃሉ።

ኢትዮጵያና ኖርዌይ ከ1939 ዓ.ም ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመስረት በሁለትዮሽና በባለብዙ መድረኮች በትብብር በመሥራት ላይ የሚገኙ ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው አገሮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም