በድሬዳዋ አስተዳደር ለውጡን ተከትሎ አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር ለውጡን ተከትሎ አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል- ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ(ኢዜአ) ጥር 20 ቀን 2015 "በድሬዳዋ አስተዳደር ለውጡን ተከትሎ በከተማዋ አስተማማኝ ሰላምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል" ሲሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ።
በድሬዳዋ ከተማ " ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለብልፅግና ጉዟችን ስኬት" በሚል መሪ ሃሳብ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመላው ሀገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘው ውይይት የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ በየደረጃው የሚገኘው ሕብረተሰብ የድርሻውን እንዲያበረከት የማስቻል አላማ ያለው ነው ተብሏል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንዳሉት፤ "በአስተዳደሩና በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተካሄደው የለውጥና የማሻሻያ ተግባራት ዘላቂ ሰላም ፣ልማትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ላይ ወሳኝ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል።"
ለውጡን ተከትሎ ከተማዋ የምስራቅ ኢትዮጵያን ክፍል የኢንዱስትሪና የንግድ መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ በከተማዋ አስተማማኝ ሰላምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በተለይ መንግስት ለሰላም መስፈን ያሳየው ቁርጠኝነት በመላው ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ዳር እንዲደርስ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኘው ሕብረተሰብ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማፅናት የተጀመረውን የዘላቂ ሰላምና የብልፅግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ የሚያደርገውን ርብርብ አጠናክሮ እንዲቀጥል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሄለን ደበበ በበኩላቸው፤ "ድሬዳዋ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ፀንቶ የተሻገረባትና ለሀገር ከፍታና ታላቅነት እርሾ የሆነች ከተማ ናት" ብለዋል።
ይህን እሴት እና ሀብት በመጠበቅና በመንከባከብ የተጀመረውን ዘላቂ ሰላም እና ልማት ዳር ማድረስ ላይ መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የፌደራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ፣የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፣ዑጋዞች፣አባገዳዎች ሴቶች፣ ወጣቶችና በየደረጃው የሚገኙ የሕብረተሰብ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።