በዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመን እስካሁን 195 ሺህ ኩንታል የተሻሻለ የምርጥ ዘር ተሰብስቧል

104

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 20 ቀን 2015 በ2014/15 የመኸር ምርት ዘመን እስካሁን 195 ሺህ ኩንታል የተሻሻለ ምርጥ ዘር መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በ2014/15 የመኸር የምርት ዘመን ለመሰብሰብ በያዘው ዕቅድ መሰረት እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

በምርት ዘመኑ 338 ሺህ ኩንታል ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ጠቅሶ፤ እስካሁን 195 ሺህ ኩንታል በመሰብሰብ በማጓጓዝ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ በራሱና በኮንትራት የምርጥ ዘር ልማትን መሸፈን ከቻለው ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ወደ መጋዘኖች እያስገባ መሆኑንም ጠቁሟል።

በዚህም በኮፈሌ ቅርንጫፍ በምዕራብ አርሲ እና በባሌ ዞኖች በግብርና ኮሌጆች እና በሰፋፊ የግል ባለሀብት እርሻ በ5 ሺህ 427 ሄክታር መሬት ላይ ያባዛውን ዘር መሰብሰቡን ገልጿል።

በኮርፖሬሽኑ የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ቡሹራ መሐመድ፤ በአርዳይታና በአጋርፋ የግብርና ኮሌጆች በተጨማሪ በባሌ ዞኖች በባለሀብቶች እርሻ ሦስት የገብስና አሥር ዓይነት የስንዴ ዝርያን በማባዛት የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ የማጓጓዝ ሥራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

እስከ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ምርት የመሰብሰብ ሥራ 50 በመቶ መከናወኑን እና 52 ሺህ ኩንታል ምርት ተረክበው ወደ ኮርፖሬሽኑ መጋዘኖች መጓጓዛቸውን ገልጸዋል።

በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የዘር ጥራት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ ጋሩማ ገመዳ፤ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የምርት መሰብሰብ ሥራ እየተፋጠነ ይገኛል ብለዋል።

በምርጥ ዘር ብዜት በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችም፤ የአርሶ አደሩ ምርታማነትን በማሳደግ በቂ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በሜካናይዜሽን ሰብል ልማትም የአርሶ አደሮች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የግል ባለሃብቶችን የምርጥ ዘር ሰብል በተመጣጣኝ ዋጋ የመሰብሰብና የማጓጓዝ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑም ተነግሯል።

በዚህም መሰረት ኮርፖሬሽኑ እስከ ጥር 17 ድረስ ለአርሶ አደሮች፣ የልማት ድርጅቶችና ባለሃብቶች 146 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቋል።

ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ የእርሻ ቦታዎች በ21 የሰብል ዓይነቶች 70 ዓይነት የምርት ዘር ማሻሻያ በማካሄድ ለአርሶ አደሮች እያቀረበ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም