ቀጥታ፡

በአገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያ ሕልውናን መታደግና ማስቀጠል ተችሏል - አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዳማ (ኢዜአ) ጥር 20/2015 “በአገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያ ሕልውና መታደግና ማስቀጠል ተችሏል” ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

“የደህንነትና የመከላከያ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ተቋማት ግንባታ የለውጡ ስኬት ማሳያ ናቸው” ብለዋል።

“ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለወንድማማችነት፤ ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ሕዝባዊ ውይይት በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።

በውይይቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተገኝተዋል።

“ለውጡ የሕዝብና በሕዝብ የመጣ ነው ፤ የለውጥ ኃይል ሁሉን አቀፍና አሳታፊ የፖለቲካ አውድ መገንባት የመጀመሪያውን እርምጃ ወስዷል” ሲሉም አፈ-ጉባኤው ገልጸዋል።

በዚህም ሂደት ውስጥ ብልጽግና ፓርቲ መመስረቱን ጠቅሰው በለውጡ ትኩረት ያገኙት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ሌሎች አገራዊ አንድምታ ያላቸው የልማት አውታሮች ቆመው ከነበሩበት ማስቀጠል መቻሉን አንስተዋል።

ሀገራዊ የተቋማት ማሻሻያና የሀገር ግንባታ የለውጡ አንድ አካል ነው ያሉት አፈ ጉባኤው በዚህም ሀገራዊ ሕልውናን መታደግና ማስቀጠል ተችሏል ነው ያሉት።

ለውጡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረው ዲፕሎማሲያዊና ወንድማዊ ግንኙነት በአግባቡ የተቃኘበትና ውጤት የተገኘበት መሆኑንና የሕግ ስርዓት ማሻሻያ፣የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ፣የፖለቲካ ምህዳር ከማስፋት አንጻር አመርቂ ውጤት መገኘቱን ነው አቶ አገኘሁ የተናገሩት።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከነበረበት ችግር በማላቀቅ ከመጀመሪያው እስከ ሶስተኛ ሙሌት ድረስ የውስጥና የዓለም አቀፉን ጫና በመቋቋም አሁን ያለበት ደረጃ መድረስ የለውጡ ውጤት አንዱና ትልቁ ማሳያ ነው ብለዋል።

"ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በመቋቋም ገረድም ውጤታማ ስራ መከናወኑንና የደህንነትና፣የመከላከያና የቴክኖሎጂ ተቋማትን የመገንባት ስራ የለውጡ ውጤት መለኪያ ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።

ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሄክታር በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል እየተከናወነ ያለው ስራ በትክክለኛ መንገድ ላይ እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን ነው አቶ አገኘሁ የገለጹት።

“ለውጡ በተለያዩ የውስጥና የውጭ ፈተናዎች የተጋረጡበት የነበረ ቢሆንም በድልና በአመርቂ ውጤት እየታጀበ ወደ ፊት እየተጓዘ ነው” ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ ከፖለቲካዊ ድል ባለፈ በመሰረተ ልማት በተለይ በትምህርት ፣በመንገድ ፣በጤናና የውሃ መሰረት ልማቶች ፣በግብርናና በተፈጥሮ ሀብት በክልሉ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል ።

በዚህም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችና መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣የተማሪዎች ምገባ ፣ የተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች ግንባታ እንዲሁም በስራ ዕድል ፈጠራ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በግብርና አበረታች ውጤት እየመጣ መሆኑን ጠቅሰው ከመኽር የስንዴ ልማት ባሻገር በበጋ ስንዴ ላይ በተሰራው ስራ ስንዴ ከውጭ ማስገባት እንዲቀር ከማስቻል ባለፈ በዘንድሮው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም