የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ሙሉ በሙሉ ማለፋቸው ተገለጸ

42

ጥር 20/2015 (ኢዜአ) የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የወሰዱ 69 ተማሪዎች መቶ በመቶ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማስመዝገባቸውን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ፈተናውን ከወሰዱት 69 ተማሪዎች ውስጥ 16ቱ 600 እና ከዚያ በላይ ውጤት ሲያመጡ 32 ተማሪዎች 500 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም 20 ተማሪዎች ደግሞ 400 እና ከዚያ በላይ እንዲሁም 1 ተማሪ ደግሞ ከ375 በላይ ውጤት በማስመዝገብ ሙሉ ለሙሉ ማለፋቸውን አብራርተዋል።

ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት “ትምህርት ቤቱን በዩኒቨርሲቲው ሥር ስንከፍት ከታች ጀምረን ህፃናቱን ብንኮተኩት ለውጤት ማብቃት፣ ሳይንቲስት ሊሆኑ የሚችሉ ትውልድን በመፍጠር ሂደት እርሾ ለመጣል እንደሚቻል ማሳያ ነው” ብለዋል።

በውጤቱ ለትምህርት ቤቱ አመራሮችና ተማሪዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት ዶክተር ብርሃነመስቀል ተማሪዎቹ በሚመደቡበት ዩኒቨርሲቲም የበለጠ ሠርተው ውጤቱን በመድገም የሜዳሊያ ባለቤት እንደሚሆኑ አልጠራጠርም ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም