በቻን ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ የሚገቡ ቀሪ ሁለት አገራት ዛሬ ይለያሉ

196

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 20/2015 ሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ማዳጋስካር ከሞዛምቢክ ፤ ኒጀር ከጋና የሩብ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የውድድሩ አስተናጋጅ አልጄሪያ እና ሴኔጋል ወደ ግማሽ ፍጻሜ ገብተዋል።

ሰባተኛው የቻን ውድድር ዛሬ 16ኛ ቀኑን ይዟል።

ከምሽቱ 1 ሰአት በመጀመሪያ የውድድሩ ተሳትፎዋ አስደናቂ ግስጋሴ በማድረግ ላይ የምትገኘው ማዳጋስካር ከሞዛምቢክ ጋር ጨዋታዋን ታደርጋለች።

የደሴቲቷ አገር በምድብ ሶስት ዘጠኝ ነጥብ በመሰብሰብ ምድቧን በበላይነት ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

በአንጻሩ ተጋጣሚዋ ሞዛምቢክ በምድብ አንድ አራት ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብታለች።

ሌላኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የምዕራብ አፍሪካ አገራቱን ጋና እና ኒጀር ከምሽቱ 4 ሰአት በሚሉድ ሀዴፊ ስታዲየም ያገናኛል።

ጋና በምድብ ሶስት በስድስት ነጥብ ማዳጋስካርን ተከትላ ከምድቧ አልፋለች።

ኒጀር ደግሞ በምድብ አምስት በአራት ነጥብ ምድቧን በመሪነት በማጠናቀቅ ነው ለሩብ ፍጻሜው ያለፈችው።

በተያያዘ ዜና ትናንት በቻን ውድድር በተደረጉ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች አዘጋጇ አገር አልጄሪያ አይሜን ማሂኡስ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በ96ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ኮትዲቭዋርን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።

በዚህ ጨዋታ ከአልጄሪያ አሌክሲስ ጉዌንዱዝ እንዲሁም ከኮትዲቭዋር ኩዋሲ ያኦ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል።

በሌላኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ላሚን ካማራ በ34ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ ሴኔጋል ሞሪታኒያን 1 ለ 0 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም