የዞኑን የቱሪስት መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ለገጽታ ግንባታና ለህዝብ ተጠቃሚነት ማዋል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዞኑን የቱሪስት መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ለገጽታ ግንባታና ለህዝብ ተጠቃሚነት ማዋል ይገባል
ደብረ ብርሃን መስከረም 24/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ለገጽታ ግንባታና ለህዝብ ተጠቃሚነት ማዋል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አሳሰበ። ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን “የዲጂታል የቴክኖሎጂ ሽግግር ለቱሪዝም ልማት!”በሚል መሪ ቃል ትናንት በአንኮበር ከተማ ተከብሯል። የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሃት በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የዞኑን ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽየቱሪስት መስህቦችን ለአገር ገጽታ ግንባታና ለህዝብ ተጠቃሚነት ማዋል ያስፈልጋል። ለዚህም ድርጅታቸውን ድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። ዞኑ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ፣የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከተስፋፉለት ጎብኚዎችን መሳብ እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል። የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሪት ትዕግስት አፈወርቅ እንደገለጹት በዞኑ ከ84 በላይ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መስህቦች እንዳሉት ገልጸው፣ከነዚህምበሚዳ ወረሞ ወረዳ የሚገኘው የመልከጼዴቅ ገዳም፣ በአንኮበር ወረዳ የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት፣ የመንዝ ጌራና የባሶና ወራና ወረዳዎች ማህበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራዎችን ለአብነት አቅርበዋል። ባለፈው ዓመት መስህቦቹን ለጎበኙት ከሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች 167ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ያወሱት ኃላፊዋ፣ ገቢው ካሉት መስህቦችና ከጎብኚዎችም ብዛት ሲታይ ግን በቂ አይደለም ብለዋል። የመሠረተ ልማት ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመሟላት፣ የምግብ፣ የአልጋና ሌሎች አገልግሎቶች ዋጋ መጨመርና የንጽህና ጉድለቶች ለችግሩ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወደ አካባቢዉ የሚመጡትን ጎብኚዎን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙ ተግባራት በጥናት ተደግፈው እንደሚከናወኑ ኃላፊዋ አስታውቀዋል።ለዚህም በቀደምት ትውልዶች ይከወኑ የነበሩ ባህላዊ ትውፊቶች ላይ በማተኮር አዳዲስ መስህቦችን ለማስገባት ይሰራል። የአንኮበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ወረዳዋ የአገሪቱ ታሪክ፣ ሥልጣኔና የዘመናዊነት አሻራዎች ያረፉባቸው የአጼ ምኒልክ ቤተ መንግሥት፣ የአልዩ አምባ ጥንታዊት የንግድ መዳረሻና የጉምሩክ ከተማ ለአውሮፓ መንግሥታት የኤምባሲ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ቦታዎች ይገኙባታል። አንኮበር ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ የደን ልማት፣ የህክምና ትምህርት፣ የስልክ መስመር ዝርጋታ፣ የፖስታ አገልግሎትና የዘመናዊ ህንፃ ግንባታ የተጀመረባት ከተማ እንደነበረች አስታውሰዋል። በአካባቢው እየተገነባ ያለው የአስፋልት መንገድ ሲጠናቀቅ የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር እንደሚያስችልም ተናግረዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን አገረ ስብከት ተወካይ ሊቀ ካህናት ዮናስ አድማሱ በበኩላቸው በዞኑ ታዋቂነት የነበራቸውን የገና ጨዋታና ሌሎች ባህላዊ እሴቶችን ለይቶ ጥቅም ላይ በማዋል ቱሪዝምን ለማስፋፋት መሥራት እንደሚያስፈግ ገልጸዋል።