ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል - አቶ መስፍን መላኩ - ኢዜአ አማርኛ
ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል - አቶ መስፍን መላኩ

ሻሸመኔ (ኢዜአ) ጥር 19 /2015 የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ሲሉ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ ተናገሩ።
አቶ መስፍን በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር በመንግስት፣ በህዝብ ተሳትፎና ከተለያዩ ምንጮች በተገኘ በጀት እየተከናወኑ ያሉ የመሰረት ልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በከተማዋ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ የሚገኘውን 'የፍጅ ሶሌ' የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማቶች ግንባታ ያሉበትን ደረጃ ተመልክተዋል።
በተጨማሪም በ471 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ለምረቃ የተቃረበውን የሻሸመኔ ከተማ መናኻሪያን የጎበኙ ሲሆን መነኻሪያው በአንድ ጊዜ 200 ተሽከርካሪዎችንና 14 ሺህ ተሳፋሪዎችን ማስተናገድ የሚችል መሆኑ ተገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ በ300 ሚሊዮን ብር እየገነባው ያለው ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ እንዲሁም የከተማ ግብርናና ለሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የሚውሉ ስራዎችንም ጎብኝተዋል።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ ከጉብኝቱ በኋላ እንደተናገሩት በተለይ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀከቱ የሻሸመኔ ከተማን ህዝብ ጥያቄን የሚመልስ ነው።
በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሂደት ለሙስናና ብልሹ አሰራሮች መንገድ የሚከፍቱ ሁኔታዎችን ማስወገድ እንደሚገባና ቀጣይነት ያለው ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻልና ገቢን ማሳደግ ሌላው ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው አስተዳደሩ በዚህ ዘርፍ የጀመረውን ስራ ማጠናከር አለበት ብለዋል።
የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ኤሌሞ በበኩላቸው በከተማዋ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው አዳዲስና ነባር ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀከቶች ግንባታ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ፣ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ፣ የመኪና ማቆሚያና መነኻሪያ እንዲሁም 'ኢፈ ቦሩ' ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም ለዘመናት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የዘገየው የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር በህዝባዊ ተሳትፎና በመንግስት በጀት ሙሉ በሙሉ እየተፈታ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ሰዓት፣ የከተማ ግብርና ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።