በአማራ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ እየተዘጋጀ ነው

227

ባህር ዳር ጥር 19 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡- በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 

በክልል ባለፈው ዓመት ክረምት በአረንጓዴ አሻራ ከተተከለው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኝ በመጀመሪያው ዙር በተደረገ ቆጠራ 83 ነጥብ 9 በመቶ መፅደቁ ተመልክቷል።  

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት፤ የችግኝ ዝግጅቱ እየተካሄደ ያለው 80 ሺህ በሚጠጉ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።  

May be an image of outdoors

የችግኝ ጣቢያዎቹ በመንግስት፣ በግል፣ በተቋማትና ማህበራት እንደተቋቋሙ ጠቅሰው፤ የተከላ ስራውም የአካባቢውን ስነ-ምህዳር መሰረት በማድረግ እንደሚከናወን አስረድተዋል። 

እስካሁን በተደረገ ጥረት ወይራ፣ ዝግባ፣ የአበሻ ፅድና ሌሎች ሀገር በቀል ችግኞችን ጨምሮ 134 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኞች ማፍላት መቻሉን ገልጸዋል።

 የችግኝ ማፍላት ሥራውም እስከ ግንቦት ወር 2015 ዓ.ም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ የችግኝ ተከላውም በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት በሚከናወንባቸው ተፋሰሶችና በሌሎች አካባቢዎች የሚከናወን ይሆናል ብለዋል።

 በመጪው ክረምት የሚከናወነው የችግኝ ተከላም የክልሉን የደን ሽፋን ከ15 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 16 በመቶ እንደሚያሳድገውም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም