በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው ልዑክ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው ልዑክ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ ጥር 19/2015 (ኢዜአ) በከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የተመራው ልዑክ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችና ዳያስፖራው በአገር ቤት በተለያዩ የኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ዘርፎች ለመሳተፍ በሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያየ።
በAfrican Mayoral Leadership Initiative (AMALI) City Leadership Forum ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የልኡካን ቡድኑ በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር ያደረገው ውይይት መረጃ መለዋወጥን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱም አገራችን በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ እንደምትገኝ፣ ለውጡም በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ድሎች እንዲመዘገቡ ዕድል መፍጠሩን ከንቲባዋ ተናግረዋል።
በተቃራኒው በለውጥ ጠል የውጭና የውስጥ ኃይሎች ሴራ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም በተጨባጭ የተረጋገጠ የሚቆጠር ዕድገት መመዝገቡንም ወይዘሮ አዳነች ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን ያወሱት ከንቲባዋ፣ በአገር ህልውና ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ በተደረገው ርብርብ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩትን ጨምሮ በሌሎች አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በዕውቀታቸው፣ በሀብታቸውና በዲፕሎማሲው ግንባር በንቃት በመሰለፍ ታሪካዊ አሻራ ማሳረፋቸውን እና አኩሪ ገድል መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት መንግስት በአገር ቤት ባመቻቸው የተለያዩ የኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ዕድሎች በውጭ ያፈሩትን ዕውቀት፣ ካፒታልና የሥራ ልምድ ተጠቅመው በአገር ቤት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተጨባጭ ተሰማርተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው በቤቶች ግንባታ፣ በቱሪዝም፣ በትምህርት እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ለመሰማራት ለሚመጡ የዳያስፖራ አባላት የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የልዑኩ አባላት የባህርዳር፣ አዳማ እና ደሴ ከተሞች ከንቲባዎች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችና ከተሞቹ ዳያስፖራውን ለማሳተፍ በሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በማስረዳት የሚመጡ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ጥያቄዎችን ተቀበሎ ለማስተናገድ ያለውን ዝግጅት በማብራራት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለቀረበላቸው ዝርዝር ገለጻና የተሳትፎ ጥሪ በማመስገን፣ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው የሚያስቀጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአገራቱ የለውጥ ጉዞ በርካታ የውስጥና የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም ተጨባጭ ትሩፋቶችን እያስገኘ የሚገኝ በመሆኑ እንዳስደሰታቸው በመግለጽ በኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ሥራዎች ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንዲሁም በሥራ እንቅስቃሴያቸው በርካታ የመልካም አስተዳደር እና ብልሹ አሰራር ችግሮች እያጋጠማቸው እንደሚገኝ በመጠቆም፤ ችግሮቹን ለመቅረፍ መንግስት በቅርቡ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።