በቻን ውድድር አልጄሪያ ከኮትዲቭዋር ሴኔጋል ከሞሪታኒያ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ይጫወታሉ

50

አዲስ አበባ (ኢዜአ)  ጥር 19/2015 ሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ዛሬ አዘጋጇ አልጄሪያ ከኮትዲቭዋር፤ ሴኔጋል ከሞሪታኒያ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የቻን ውድድር ዛሬ 15ኛ ቀኑን ይዟል።

ውድድሩ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ይመለሳል።

የውድድሩ አስተናጋጅ አልጄሪያ በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ከምሽቱ 1 ሰአት ከኮትዲቭዋር ጋር የምታደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።

አልጄሪያ በምድብ አንድ ያደረገቻቸውን ሶስት ጨዋታዎች በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ ምድቧን በመሪነት በማጠናቀቅ ለሩብ ፍጻሜው ማለፏ ይታወቃል።

ተጋጣሚዋ ኮትዲቭዋር በምድብ ሁለት በሶስት ጨዋታ አራት ነጥቦችን በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በሌላኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰአት ሴኔጋል ከሞሪታኒያ በ ‘19 May 1956’ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሴኔጋል በምድብ አንድ እንዲሁም በምድብ አራት ሞሪታኒያ ምድባቸውን በመሪነት ማጠናቀቃቸው ይታወቃል።

በተያያዘም የቻን ውድድር የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ ማዳጋስካር ከሞዛምቢክ፤ ኒጀር ከጋና ይጫወታሉ።

የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አሸናፊዎች የፊታችን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም