የምስጋናና የስጦታ መድረክ - ዳራሮ

49

ያንተስራ ወጋየሁ (ኢዜአ - ዲላ)

ጌዴኦ በባህላዊ የባሌ አስተዳደር ሥርዓት በየስምንት ዓመቱ የሚቀያየር አባገዳ መርጦ የሚተዳደር ህዝብ ነው።

“ባሌ” የህዝቡን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በበላይነት እየመራ ላለፉት 500 ዓመታት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገር የመጣ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት መሆኑ ይነገራል።

"ዳራሮ" የስርዓቱ መሪ የሆኑት አባገዳ በዓመት አንድ ጊዜ የሚጠሩት የጌዴኦ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ነው።

የጌዴኦ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ዶክተር ዮሴፍ ማሩ ዳራሮ ከዘመን መለወጫነቱ በተጓዳኝ ጌዴኦ ቀዬ መንደሩን ሰላም ላደረገ፣ አዝመራና ሰብሉን ከተምች ለጠበቀ፣ ህዝቡንና ምድሩን ከመዓትና እርግማን ለታደገ ማጎኖ /ፈጣሪ/ ምስጋና የሚያቀርብበት እንዲሁም ለአባገዳ ስጦታ የሚሰጥበት ቀን ነው።

ከዚህም ባለፈ ዳራሮ ጌዴኦ በባህላዊ የአስተዳደር ታሪኩ ካለፋቸው አሃዳዊ ከሆኑ “የአኮማኖዬና” ተከትሎም ከመጣው “የጎሳሎ” ሥረወ መንግስታት በተደረገ የህዝብ ትግል ተላቆ አካታችና አሳታፊ ወደ ሆነው የባሌ ስርዓት የተሸጋገረበት የነጻነት ቀኑ ጭምር ነው ሲሉ ያብራራሉ።

የዳራሮ በዓል የምስጋና የስጦታና ሌሎች ጠቃሚ እሴቶቹ ለህዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ሰላም አስተዋጽኦው የጎላ በመሆኑ በዓሉ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ እየተሰራ መሆኑንም ይናገራሉ።

ዳራሮ በየዓመቱ በጌዴኦ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር መሰረት ከታህሳስ መጨረሻዎቹ ቀናት አንስቶ እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ ባሉ ቀናት በአንዱ ቀን የሚከበር በዓል ነው።

ወቅቱ አርሶ አደሩ የቡና፣ የገብስና መሰል የግብርና ምርቶቹን ሰብስቦ ለቀጣይ ምርት የሚሰናዳበት መሆኑን የሚናገሩት ሃላፊው፤ ቀኑ መግባቱንም ተከትሎ በዞኑ በሚገኙት ሶስት ባህላዊ አካባቢዎችና 554 የመንደር ሸንጎዎች አባገዳው ዳራሮን በየትኛው ቀን ጠሩ ወይም እንዲውል አዘዙ የሚል መረጃ በስፋት መነገር ይጀመራል።

የወንዞች መጉደል፣ የወርሃ ታህሳስ እምቡጥ አበቦች፣ ቁልቁል የሚፈሱ ፏፏቴዎች ቀጭን ድምጽ ውብ አበቦችን ቀስመው የሰበሰቡት ማር ቤታቸውን ስለሚሞላ እባካችሁን ተረከቡን ከሚል የንቦች ጥሪ ጋር ተዳምሮ ዳራሮ ደረስኩ ደረስኩ ማለቱን እራሱ ተፈጥሮ መናገር ይጀምራል።

በተለይ እስከ ጥር 10 ባሉት ቀናት ውስጥ በብሔሩ አጠራር “አርፋሳ” ተብሎ የሚታወቀው ዝናብና ካፊያ መጣል መጀመሩን ተከትሎ የበዓሉ ቀን መቃረቡን ስለሚጠቁም ህዝቡ ቀኑን የማወቅ ጉጉቱ በእጅጉ ያይላል።

በዚህም ጊዜ ይላሉ ዶክተር ዮሴፍ ማሩ፤ አባገዳው በተዋረድ የሚገኙ የሥርዓቱ መሪዎችን ወደ መናገሻቸው በመጥራት አርሶ አደሩ ፍሬውን አዝመራና ሰብሉን ሰብስቦ መጨረሱን ካረጋገጡ በኋላ ቀኑን በባህላዊ አቆጣጠር የጨረቃና ከዋክብት መግባትና መውጣትን በመመልከት በጥንቃቄ በመለየት ዳራሮን በይፋ ያውጃሉ።

ቀኑን ቀድሞ መስማት በህብረተሰቡ ዘንድ በረከት ተደርጎ ስለሚወሰድ የሰማው ላልሰማው እያቀበለ ወሬው ከዳር ዳር ይደርሳል።

በእለቱም አርሶ አደሩ በጎተራው ካከማቸው ቡና፣ የእህልና የጥራጥሬ እንዲሁም ከማር ምርቱ ለአባገዳው የሚሆን ጉማታ ወይም ስጦታ ሸክፎ አባገዳውን በሚያሞግስ ዜማ ወይም “ቄጣላ” እየጨፈረ በዓሉ ወደ ሚከበርበት “ኦዳ ያአ ሶንጎ” ከየአቅጣጫው ይተማል።

ከእለቱም አንድ ቀን ቀድሞ አባገዳውን ጨምሮ በተዋረድ የሚገኙ የሥርዓቱ ሽማግሌዎች የዳራሮ በዓል አንድ አካል የሆነውን የንሰሃ “የፋጪኤ” ሰርዓት እያከናወኑ ያድራሉ።

በዚያም በዓመቱ የታዩ ኃጥያቶችንና የክፋት ስራዎችን ፈጣሪ ህዝቡንና ምድሩን ይቅር እንዲላቸው ይለምናሉ።

በንጋታውም የንስሃ “የፋጪኤ” ስርዓት መጠናቀቁን ተከትሎ አባገዳው ከሥርዓቱ ሽማግሌዎች ጋር ወደ ”ኦዳ ያአ ሶንጎ” ያቀናሉ።

ከየአቅጣጫውም የሚመጣው ህዝብ ከአባገዳውና ከሥርዓቱ ሽማግሌዎች ጀርባ በመሆን በጭፈራ፣ በሆይታ፣ በእልልታ ያቀናሉ።

ቀድመው “ኦዳ ያአ ሶንጎ” የደረሱ ሰዎችም ቢሆኑ የአባገዳውና የስርዓቱ መሪ የሆኑ የሽማግሌዎችን በቦታው መድረስ ሲያዩ ከፍተኛ ደስታና ፈንጠዚያ በዛ ይሆናል፤ ጎን ለጎንም የተራራቁ ሰዎች ይገናኛሉ የተኮራረፉ ይታረቃሉ።

ዳራሮ ሁሌም ቢሆን የሚጀምረው “ፋጎ” በተሰኘ የብሔሩ መዝሙር ነው። “ፋጎ” የብሔሩ መለያ የሆነ ከጥንት ጀመሮ የመጣ የህዝብ መዝሙር ነው።

በመዝሙሩ የብሔር አመጣጥና አሰፋፈር ይዘክራል፤ ተስፋቸውንና እድገታቸውን ሙዚቃዊ በሆነ መንገድ ይገለጻል ስራ ወዳድና ጀግና መሆናቸውም ያሳውቃሉ ይፎክራሉ፣ ያቅራራሉ።

የሥርዓቱ ሽማግሌዎች እየተቀባበሉ ሲያቀነቅኑ የተቀረው ህዝብ እየተቀበለ በደማቅ ሁኔታ ያዜማል።

መዝሙሩ በጋራ እየተባለ ከለምለም ሃረግ፣ ከዘንባባና ከቀርካሃ በተሰራ መተላለፊያ ውስጥ ያልፋሉ።

ይህም ያለፈውን ዓመት ትቶ ወደ አዲስ ዓመት የመሻገር ተምሳሌት ተደርጎ ይወስዳል።

ህዝቡም አባገዳውንና ሽማግሌዎችን ተከትሎ ሶስት ጊዜ ይሾልካል የዛኔም አዲስ ዓመት ገባ ይባላል።

አዲስ ዓመት መግባቱንም ተከትሎ ዳራሮ የተሰኘውን ምግብና ከንጹ ማር የተሰራውን “ቦካ” የተሰኘ መጠጥ አባገዳውና የሥርዓቱ ሽማግሌዎች መርቀው ለህዝብ ያከፋፍላሉ።

በዚህም ጊዜ የወጣው ህዝቡ ሁሉ ዳራሮ የተሰኘውን ምግብ ከአባገዳ እጅ ለመቀበል ያለው ትንቅንቅ በእጅጉ ቀልብ ይስባል።

ዳራሮ የተሰኘውን ምግብ ከአባገዳ እጅ ተቀብሎ ብቻ አይመለስም። የሸከፈውን ጉማታ ወይም ስጦታ በመስጠት ከአባገዳውና ከሽማግሌዎች ምርቃት ይቀበላል።

አባገዳ ለህዝብ የተሰጡ በመሆናቸው አያርሱም አይነግዱም ብቸኛው የገቢ ምንጫቸው በዳራሮ በዓል ጊዜ የሚበረከትላቸው የፍቅር ስጦታ ነው ይላሉ የባህልና ቅርስ ተመራማሪው እጩ ዶክተር ጸጋዬ ታደሰ።

አባገዳም ጉማታ ወይም ስጦታቸውን ተቀብለው ህዝብ ይመርቃሉ።

ህዝቡም ለምለም ሳር ይዞ በዜማ ምርቃቱን ይቀበላል። የዳራሮ በዓል ማሳረጊያውም ህግ የመደንገግ ሥርዓት ነው።

ይህም በብሔሩ አጠራር “ላላባ” ይባላል ትርጓሜውም አዋጅ ማለት ነው።

የስርዓቱ መሪ የሆኑት አባገዳ በጠቅላላ ጉባኤዎች በአመቱ የታዩ ክፍቶችንና ከሥርዓትና ከባህል የወጡ ጉዳዮችን በመለየት ዳግም እንዳይፈጸሙ ክልከላ ያስቀምጣሉ አዋጅ ይደነግጋሉ።

ለአብነትም ጥሎሽ በዝቶ ማህበራዊ ሕይወት ላይ ጫና ካሳደረ፤ ዛፍ መቁረጥ ከተበራከት በአባገዳው አዋጅ ወጥቶ ክልከላና ገደብ ይቀመጣል ማለት ነው።

አዋጁም በሶስቱ ባህላዊ አካባቢዎችና በ554 የአካባቢ ሸንጎዎች በተደጋጋሚ እንዲነገር ይደረጋል።

ህዝብ አክብረው ኦዳ ያአ ሶንጎ የወጡት አባገዳም መናገሻቸው እስኪመለሱ ድረስ ይጨፈራል የአባቶች ፉከራና ቀረርቶ ልዩ ነው የልጆች ፈንጠዝያም ቀልብ ይስበል።

የዘንድሮው የዳራሮ በዓል በአባ ገዳ መናገሻ ኦዳ ያአ ሶንጎ መከበር የጀመረ ሲሆን በነገው ዕለት የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት የዞኑ መዲና በሆነችው ዲላ ከተማ በታላቅ ድምቀት የሚጠቃለል መሆኑ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም