ታዳጊ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ መስጠት የሚችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ አቅምን መገንባት ያስፈልጋቸዋል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ታዳጊ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ መስጠት የሚችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ አቅምን መገንባት ያስፈልጋቸዋል - ምሁራን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 19/2015 ታዳጊ አገራት በዓለም ላይ ጫና እያሳደረ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምላሽ መስጠት የሚችል የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልጋቸው የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የምታካሂደው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታም አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የግብርና፣ የምግብ እንዲሁም የተፈጥሮ ጥበቃና የውሃ ኢነርጂ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚል አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር አበበ ጌታሁን በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው።
በዚህም የአየር ብክለትና በረሃማነት፣ ድርቅና ርሃብ፣ ጎርፍና ቅዝቃዜ በማስከተል በዓለም ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ አደጋ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የማይችሉ እጽዋትና እንስሳት እንዲጠፉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የውሃ፣ የንፋስ እና የፀሐይ ታዳሽ የኃይል ማመንጫ ልማትን አጠናክሮ በማስቀጠል ለተፅዕኖው ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጥበቃና አስተዳደር ፕሮፌሰር ዘውዱ እሸቱ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ታዳጊ አገራት ተፅዕኖውን መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅም ባለመገንባታቸው ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የታዳጊ አገራት የኢኮኖሚ መሰረት ግብርና በመሆኑም አየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ አድርጓቸዋል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ለዚህም አማራጭ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው አክለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ የውሃ ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፈለቀ ዘውገ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ በታዳሽ ኃይል የተመሰረተ ኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እና ታዳሽ የኃይል አማራጭ ልማቶች የሚበረታቱና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ተግባራት እንደሆኑ ገልጸዋል።
በቀጣይም የሕብረተሰቡን የባለቤትነት ስሜት በማሳደግ በጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም በፖሊሲ የተደገፈ የደን ልማት ሥራን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር መንሱር ደሴ፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መነሻ በማድረግ ለተፅዕኖው ምላሽ እየሰጠች ነው ብለዋል።
ለዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ዕቅድ፣ ስትራቴጂና ፖሊሲ በመቅረጽ ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ምንም እንኳን የዓለም መንግሥታት እና የዓለም ሕዝብ በትብብር ካልሰሩ ተፈጻሚነቱ ላይ ጥያቄ ቢነሳበትም አገራት እ. አ. አ . በ2050 የካርበን ልቀት መጠንን ዜሮ ለማድረግ መስማማታቸው ይታወሳል።
ዓለም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን በ1 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ በማለቱ ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበንይኦክሳይድ መጠንም 50 በመቶ እንዲጨምር አድርጎታል።