ከ100 ሺህ በላይ እንግዶችን ቡና የማጠጣት መርሃ ግብር በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው

208

ዲላ (ኢዜአ) ጥር 19/2015 ከ100 ሺህ በላይ እንግዶችና ደራሮ የጌድኦ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ታዳሚዎችን ቡና የማጠጣት መርሃ-ግብር በዲላ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋዬ እንዳሉት ከቡና መገኛነታችን በተጨማሪ ቡናን ከአፈላል ጀምሮ መጠጫው ላይ ያሉ ስርዓቶችን ለማህበራዊ ትስስርና ለአብሮነት መጠናከር ያለውን ፋይዳ ማስተዋወቅ ይገባናል።

የጌዴኦ ዞን ከደራሮ በዓል ጋር አስተሳስሮ ከ20 ሺህ የሚልበጡ ሲኒዎችን በመደርደር የቡና ጠጡ መርሃ ግብር ማዘጋጀታቸው አምራችነታችንና ለቡና ያለንን ባህላዊ ትስስር በግልጽ የሚያሳይ ነውም ብለዋል።

ይኸንን የቡና አፈላልና አጠጣጥ ስርዓታችንን በማስፋት ለቱሪስት መስህብነት ልንገለገልበትም ይገባል ነው ያሉት።

የጌዴኦ ህዝብ ተፈጥሮን ከባህሉ ጋር የሚያስታርቅበት ባህላዊ እሴቶቹን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በክልል ደረጃ የተለያዩ ጥናቶች እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል።

በተለይም የጌዴኦ ባህላዊ ትሩፋቶች ከሆኑት መካከል የአከባቢ ጥበቃ ባህሉ ለግብርና ልማትና ለምግብ ዋስትና ያለውን አስተዋጾ ለማጉላት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩለቸው የቡና ጠጡ መርሃ ግበሩ ካለፉት ሶስት ዓመት ወዲህ የዞኑ ዓመታዊ የደራሮ በዓል ጋር አብሮ ሲካሄድ ቆይቷል።

ከዓመት ዓመት እያደገ በመጣው በዚሁ ባህላዊ የቡና ጠጡ መርሃ ግብር በዘንድሮው ደራሮ ከ20 ሺህ በላይ ሲኒዎች የተደረደሩበት ሰፊ ረከቦት ለማዘጋጀት መብቃቱንም ተናግረዋል።

ቡና በሀገራችን በሁሉም አከባቢ በሚባል ደረጃ በሚጠጣበት ወቅት የሚፈጠረው አብሮነት ለሀገራዊ አንድነት መጠናከርም የራሱ ድርሻ እንዳለው አክለዋል።

ይህም የዞኑን የቡና አምራችነት ከማስተዋወቅ ባለፈ ቡና በሚፈላበትና በሚጠጣበት ወቅት የሚፈጥረውን መቀራረብና አንድነት በማጉላት ወደ ታላቅ ፌስትቫልነት ማሳደግና ለቱሪዝም መዳረሻነት ሊያገለግል ይገባል ነው ያሉት።

የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ ወይዘሮ ዜና ማሞ ለኢዜአ እንዳሉት ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የቡና ጠጡ መርሃ ግብር ከ100 ሺህ በላይ እንግዶችና የበዓሉ ታዳሚዎች አንድ ሲኒ ቡና በነጻ የማጠጣት ዕቅድ ተይዞ በመካሄድ ላይ ነው።

ይህም በሀገር ደረጃ ያለንን ቡናችንንና ባህላዊ አፈላላችንን በማስተዋወቅ ለበዓሉ የተለዬ ድምቀት መፍጠሩን አስረድተዋል።

በዚህ የቡና ጠጡ መርሃ ግብር ከአምራች አርሶ አደሮች የተገኘ ከ200 ኪሎ ግራም በላይ ቡና አገልግሎት ላይ መዋሉንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ በቡና አምራችነት የምትታወቅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ባህላዊ የቡና አፈላልና አጠጣጥ ስርዓታችንም በዚሁ ልክ መተዋወቅና የቱሪዝም መዳረሻ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ዳራሮ የአደባባይ በዓል በመሆኑ ባህላዊ የቡና አፈላል ስርዓታችንን አደባባይ በማውጣት አንድነታችንን ማጠናከር ችለናል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ ወይዘሮ ሙሉ ዋቆ ናቸው።

በተለይም ቡናን አምርቶ ለአለም ገበያ ከማቅረብ ባለፈ አጠቃቀሙንም በማስተዋወቅ ተቀባይነቱን ማሳደግ እንደሚገባም በማከል።

የጌዴኦ ብሄር የዘመን መለወጫ የበራሮ በዓል አንዱ መርሃ ግብር የሆነው የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየምም በመካሄድ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም