ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ የጋራ ትብብርና ጥረት አስፈላጊ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ የጋራ ትብብርና ጥረት አስፈላጊ ነው
ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ጥር 18/2015 በሁሉም አካባቢ ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ የጋራ ትብብርና ጥረት አስፈላጊ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።
የ"ኢትዮጵያ ታምርት ፎረም" ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በፎረሙ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፣ የለውጥ ስርዓቱ ከመጣ ወዲህ ክልሉ ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
በዚህም በየዓመቱ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ወደክልሉ መጥተው መዋዕለንዋያቸውን በማፍሰስ ራሳቸውን ከመጥቀም ባሻገር ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።
"ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ሰላምና መረጋጋት ይጠይቃል" ያሉት ዶክተር ይልቃል፣ ሰላምን ለማስፈን ደግሞ የጋራ ትብብርና ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢኮኖሚውን በዘላቂነት ለመገንባት የሚያስችሉ አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን ፈጥሮ በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ይልቃል ገለጻ፣ "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል ንቅናቄ የተዘረጋው አገር በቀል ኢኮኖሚም በክልሉ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እንቅስቃሴ የሚያበረታታና ተስፋ የሚሰጥ ነው።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ ያለውን ሃብትና ጸጋ አሟጦ በማልማት ለህዝብ ጥቅም ማዋል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
"በእዚህም የግል ባለሃብቱ ዋነኛ ተዋናይ እንዲሆን መደገፍና ማበረታታት ይገባል" ያሉት ቢሮ ሃላፊው፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በማሳካት የሀገሪቱን እድገትና ብልጽግና ለማፋጠን መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።
በክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ለባለሀብቱ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ለመዘርጋት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ እንድሪስ እንዳሉት በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ከ60 በላይ ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት ሥራ ተሸጋግረዋል።
በክልሉ ፈጥኖ ወደ ማምረት ለመሻገገር የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና የኢንዱስትሪ መንደሮች ተገንብተው ለባለሃብቱ ክፍት መደረጋቸውንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ መጥተው ኢንቨስት ቢያደርጉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደማይላቸው ቢሮ ሀላፊው አረጋግጠዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች እና አገልግሎት ዘርፉን በማሳተፍ ከተካሄደው የ''ኢትዮጵያ ታምርት ፎረም'' በተጨማሪ ኢንዱስትሪዎችና ምርቶቻቸው ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ተጎብኝቷል።