በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት 1ሺህ 660 ሜጋ ዋት ሃይል ከንፋስና ከጸሐይ የሚያመነጩ ጣቢያዎችን ለመገንባት ታቅዷል--የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል

230

አዲስ አበባ ጥር 18/2015 (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት 1ሺህ 660 ሜጋ ዋት ሃይል ከንፋስና ከጸሐይ የሚያመነጩ ጣቢያዎችን ግንባታ ለመጀመር መታቀዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።

የኤሌክትሪክ ሃይሉ በሶስት ዓመት መሪ የተቋሙ ዕቅድ ዙሪያ ዛሬ ከሰራተኞቹ ጋር ውይይት አድርጓል።

የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አንዱዓለም ሲያ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በውሃ ሃይል ማመንጫ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተው የሀገሪቱ የሃይል ዘርፍ በተደጋጋሚ በሚከሰት የአየር ሁኔታ መለዋወጥ ሳቢያ የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ እንደሚያጋጥም ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከውሃ ሃይል ማመንጫ ባሻገር ሌሎች የታዳሽ ሃይል ማመንጫ አማራጮችን በስፋት መጠቀም አይነተኛ መፍተሄ መሆኑን የገለጹት ስራ አስፈጻሚው ተቋሙ በዚህ ዙሪያ የሶስት ዓመታት መሪ እቅድ ማዘጋጀቱን አረድተዋል።

እንደ ሀገር የንፋስ ፣የጸሐይ እንዲሁም የከርሰ ምድር እንፋሎት ሃይል ማመንጫ አማራጮችን በስፋት ለመጠቀም አቅም መኖሩንና አዋጪ መሀኖቸውም በጥናት መረጋገጡን ነው የገለጹት።

ጥናቱን መሰረት በማድረግም በሶስት ዓመታት ውስጥ በአስር የተለያዩ አካባቢዎች የንፋስና የጸሐይ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ለመገንባት እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

በተለይ በድሬደዋ፣ጋድ፣ወረንሶ፣አዲጋላ፣መተሃራ፣አንዲሁም አይሻ አካባቢዎች አዳዲስ የንፋስና የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ለመገንባት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩ ተቋሙ አረጋግጧል ብለዋል።

May be an image of 1 person, sitting, standing and indoor

የሚገነቡት የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ሁሉም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ማዕቀፍ ውስጥ በግሉ ዘርፍ እንደሚገነቡ ጠቅሰው ከተለያዩ ባለሃብቶች ጋር ውይይቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

አዳዲስ የሚገነቡት የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለሀገሪቱ የሃይል ዘርፍ እድገት ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው አብራርተው ከሃይል ማመንጫ ከጣቢያዎቹ 1ሺህ 660 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ሃይል ማመንጨት እንደሚቻልም ገልጸዋል።

የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ ለሀገሪቱ ከሚያስገኙት የሃይል እድገት በተጨማሪ ለጎረቤት ሃገራት በመላክ ከሃገራቱ ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጎልበት ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመው በሶስት ዓመታት ውስጥ ተሰርተው ወደ ተግባር የሚገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም