ፌዴሬሽኑ ለ13ኛው የአዲስ አበባ ዋንጫ ስኬት ዝግጅቱን አጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴሬሽኑ ለ13ኛው የአዲስ አበባ ዋንጫ ስኬት ዝግጅቱን አጠናቋል
አዲስ አበባ መስከረም 24/2011 በተያዘው ወር ማብቂያ የሚጀመረውን የአዲስ አበባ ዋንጫ በሠላማዊ ሁኔታ ለማካሄድ መዘጋጀቱን የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አስታወቀ። የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የሲቲ ካፕ ውድድር ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ነው የሚካሄደው። ውድድሩ መስከረም 26 ቀን 2011 ዓ.ም የሚጀመር ሲሆን እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ይዘልቃል። የሲቲ ካፕ ውድድሮች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ አስቀድሞ የክልል ፌዴሬሽኖች የሚያዘጋጇዋቸው ናቸው። የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አያሌው ታደለ ለኢዜአ እንደገለጹት ውድድሩ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል። በ12ኛው የሲቲ ካፕ ውድድር ላይ በደጋፊዎች መካከል ተከስቶ የነበረው አይነት የጸጥታ ችግር እንዳይደገም ለማድረግ የጸጥታ ኮሚቴ መደራጀቱንም ነው የተናገሩት። ስምንት ክለቦች የሚሳተፉበት የዘንድሮው ውድድር የምስራቅ አፍሪካ ተጋባዥ ክለብ የሚካፈልበት መሆኑ ከሌላው ጊዜ ለየት እንደሚያደርገውም ገልጸዋል። ኳራ ዩናይትድ የተሰኘ የናይጄሪያ ክለብ በውድድሩ የሚሳተፍ መሆኑን በመጥቀስ። ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ እና ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ አዲስ አበባን ወክለው ይሳተፋሉ። ወላይታ ዲቻ፣ ጅማ አባጅፋርና አዳማ ከተማ ከክልል ተጋባዥ ክለቦች መካከል ይገኙበታል። የውድድሩ የአምስት ጊዜ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ስለሚያዋጣ በውድድሩ ለመሳተፍ በቂ ስብስብ አይኖረኝም በማለት እንደማይሳተፍ ቢያሳውቅም ወደ ውድድሩ ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግ አቶ አያሌው ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በተካሄደው የከተማ ዋንጫ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን ዘንድሮ 6 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል። የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ውድድሩ በሰላምና በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የእግር ኳስ ቤተሰቡ እንዲተባበርም ጥሪ አስተላልፈዋል።