ቀጥታ፡

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ለጎርፍ መከላከል ፕሮጀክቶች የሚውል 745 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 18 ቀን 2015 የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ለጎርፍ መከላከል ፕሮጀክቶች የሚውል የ745 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ሥምምነት አደረገ።

ለአራት ዓመታት በሚተገበሩት ሁለቱ ፕሮጀክቶች በድምሩ ከ55 ሚሊየን ዜጎች በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተገልጿል።  

የድጋፍ ሥምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ዑስማን ዳዮኔ ተፈራርመዋል።  

በድጋፍ የተገኘው ገንዘብም ለጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ለጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ተግባር የሚውል መሆኑ ተገልጿል። 

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በአየር ንብረት ለውጥና በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍና እገዛ ለማድረግ መወሰኑን ዳይሬክተሩ ዑስማን ዳዮኔ ተናግረዋል። 

በዚህም 445 ሚሊየን ዶላሩ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን ጨምሮ ለተፈናቀሉ ዜጎች ህይወት አድን አገልግሎት ማቅረብ በሚያስችሉ የመጀመሪያ ደረጃ መሰረታዊና ፍትሕዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንደሚውል ገልጸዋል። 

ቀሪው 300 ሚሊዮን ዶላር ደግም የጎርፍ አደጋን የመከላከል ፕሮጀክቶች እንደሚውል ገልጸው፤ ተጋላጭነትን ለመቀነስና ተጽዕኖን መቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል። 

በመሆኑም በአዋሽ፣ ኦሞና ስምጥ ሸለቆ ሐይቅ ተፋሰሶችን ጨምሮ በተመረጡ አካባቢዎች ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል። 

በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለተፈተኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊንን ከቀውስ ለመታደግ ፕሮጀክቱ አጋዥ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

 የሁለቱ ፕሮጀክት ክንውን በጤናው ዘርፍ ከ22 ሚሊየን፣ በጎርፍ አደጋ መከላከል ፕሮጀክት 34 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቅሰው የዓለም ባንክ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የድጋፍ ሥምምነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሜሪካ ባቀኑበት ወቅት ከባንኩ ኃላፊ ጋር ባደረጉት ውይይት ቃል የተገባ መሆኑን አስታውሰዋል። 

ድጋፉም በመሠረታዊ ጤና አገልግሎት ተደራሽነትና በግጭቱ የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።

 ሁለተኛው ፕሮጀክት ደግሞ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ላይ የመከላከል መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ትንበያ አቅምን ለመገንባት ይውላል ብለዋል።

 በዚህም የአደጋ ተጽዕኖ መቋቋም አቅምን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ገልፀው፤ ሁለቱ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራዎችን ለመደገፍ ሁነኛ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል።

 የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ ሁነኛ አጋር ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው በቀጣይም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ግንባታና ማቋቋም ሥራዎች ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። 

የዓለም አቀፍ ልማት ማኅበር በሚል ማዕቀፍ ድጋፉ የተደረገ ሲሆን በጤና ሚኒስቴርና በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትብብር እንደሚፈጸም ተገልጿል።

 የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ድጋፉ በተለይም መልሶ ግንባታው የሚሰሩ መንግሥታዊ ጥረቶችን የሚያግዝ፤ የጤና አገልግሎትና ጥራትና ተደራሽነት ላይ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል። 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢኒጂነር ኃብታሙ ኢተፋም ድጋፉ መንግሥት ትኩረት በሰጣባቸው ዘርፈች አንዱ በሆነው በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢ ማኅበረሰበብ በተፈጥሮ አደጋ መቋቋምና ዘላቂነት የማቋቋም ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። 

ሁለቱ ሚኒስቴሮች ፕሮጀክቱ ትግበራና ውጤታማነት ከአጋር አካላት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። 

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1960 የተቋቋመው የአለም ባንክ አለም አቀፍ ልማት ማህበር (አይ.ዲ.ኤ) ድሃ በሆኑ አገራት ኢኮኖሚያቸውን የሚያሻሽል፣ ድህነትን የሚቀንስና የማኅበረሰቡን ሕይወት ለሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች በአነስተኛ ወለድ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ የፋይናንስ ተቋም ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም