ቀጥታ፡

የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

ደሴ፣ ጥር 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) በህክምና ተቋማት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሻሻል ተገልጋዩ ህብረተሰብ የተሟላ የጤና አገልግሎት በጥራትና በፍጥነት እንዲያገኝ ለማስቻል በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

11ኛው የኢትዮጵያ ህክምና ትምህርት ቤቶች ካውንስል ጉባኤ በወሎ ዩኒቨርሲቲና በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የጤና ተደራሽነቱን ለማስፋት በተደረገ ጥረት ውጤት ቢመዘገብም በጥራትና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ አሁንም ተግዳሮቶች አሉ፡፡

ጤና ጣቢያና ጤና ኬላዎችን በመገንባት ህብረተሰቡ በቅርበት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ ቢሆንም የአገልግሎት ጥራት መጓደል ችግር በሚፈለገው ልክ ሊፈታ እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ ለተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲሰጡ በማድረግ በስነ ምግባርና በክህሎት የጎለበተ የሰው ኃይል ለማፍራት በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በቴክኖሎጂ ጭምር ታግዞ ሙያውን አክብሮና በተመደበበት ቦታ በተሟላ ብቃትና ጥራት የሚሠራ ትውልድ ለማፍራት ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በየዓመቱ የህክምና ትምህርት ቤቶች ካውንስል ጉባኤ በማካሄድ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ ችግሮችን በጥናትና ምርምር እንዲፈቱ፣ ለባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ብቃትና ምዘና እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና ተማሪዎች ልማት ዴስክ ኃላፊ አቶ በየነ ተዘራ በበኩላቸው የጤና አገልግሎት ጥራትን በማስጠበቅ ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ሚኒስቴሩ የድርሻውን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸዋል።

ህክምና ከሰው ህይወት ጋር የተገናኘ ጥንቃቄ የሚሻ ሙያ በመሆኑ ለተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲሰጥ ከማድረግ ባለፈ ለትምህርት ወደ ሙያው ሲገቡናሲያጠናቅቁ ሙያዊ ፈተና ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

በሚማሩበት ተቋም በቂ ግብዓት እንዲሟላ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያዊ መልካም ስነ ምግባር እንዲታነጹም በትምህርት ፖሊሲው ላይ ማሻሻያ በማድረግ እየተተገበረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

''የተማሪዎችን ቁጥር በመቀነስ ተግባር ተኮር ትምህርት በጥራት መስጠት ጀምረናል፣ በቂ ግብዓትም እያሟላን ነው'' ያሉት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር መታደል አዳነ ናቸው፡፡

የጤናውን ዘርፍ ስርዓት፣ ጥራትና አገልግሎት ለማሻሻልም ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ፈንታሁን ድረስ በበኩላቸው፤ በካውንስል ጉባኤው የልምድ ልውውጥ በማድረግ፣ ችግሮችን በጥናት ጭምር በመለየት ግብዓት እያገኘን ነው ብለዋል፡፡

በተግባር ተኮር ትምህርት ብቁ ዜጋ ለማፍራት ለጤና ትምህርት ክፍል በተሰጠው ትኩረት የተገኘውን ለውጥ ለሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሞክሮ ማጋራት መቻሉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም