ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አድርጋለች- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 18 ቀን 2015 በአዲስ አበባ የሚካሄደው 36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የመሪዎች ጉባዔ በአህጉሪቷ የፖለቲካ፣ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ማህበራዊና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት እንደሚመክር ይጠበቃል።

36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና 42ኛው የህብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ "የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ማፋጠን" በሚል መሪ ሃሳብ ከየካቲት 8 እስከ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኢትዮጵያ ጉባዔውን በስኬት ለማጠናቀቅ እያደረገች ያለውን ዝግጅት በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከ30 በላይ ተቋማት የተካተቱበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን ጀምሯል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር አየለ ሊሬ፤ የዘንድሮው የመሪዎች ጉባዔ አጀንዳ 2063 ገቢራዊ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ይዳሰስበታል ብለዋል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የተሰሩ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮችን የቀጣይ ዕቅዶች በዝርዝር ይዳሰሱበታልም ነው ያሉት።

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አፍሪካን በኢኮኖሚና ንግድ ለማቀራረብና የእርስ በርስ ግንኙነቱን ለማጎልበት ምን መደረግ እንዳለበት ይመክራልም ብለዋል፡፡

አፍሪካውያን በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በጋራና በተናጠል ምን መሥራት እንዳለባቸው እንደሚወያዩ ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በጫና ውስጥ ሆና በስኬት ማስተናገዷን ገልጸዋል፡፡

"ዘንድሮም እንደ አዘጋጅ ሀገር የመሪነት ኃላፊነታችንን በመወጣት ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ኃላፊነቶችን በብቃት መወጣት እንደምንችል የምናሳይበት ዝግጅት አድርገናል" ብለዋል፡፡

ከተለያዩ አገልግሎቶች ከሚገኝ የውጭ ምንዛሬ ሀገርን በኢኮኖሚ መደገፍ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጉዳዮችን በማስተዋወቅ ገጽታን መገንባት የምንችልበት ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ባሻገር በአረንጓዴ አሻራና በፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ዙሪያ ሦስት የሚሆኑ የጎንዮሽ ውይይቶች የማድረግ ዕቅድ እንዳላትም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም