የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ይፋ ተደረገ

ጥር 18/ 2015 (ኢዜአ) የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የሲሚንቶ አምራቾች ቦርድ አዲሱን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ይፋ አደረጉ።
አዲሱን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ አስመልክቶ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የሲሚንቶ አምራቾች ቦርድ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
መግለጫውን የሰጡት የሲሚንቶ አምራቾች ቦርድ ሰብሳቢ አዱኛ በቀለ፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲሚንቶ በአዲሱ የዋጋ መሸጫ ተመን መሰረት ይሰራጫል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሲሚንቶ ላይ የነበረው ቁጥጥር ከተነሳ በኋላ የተሻለ የምርት ሥርጭት እየታየ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለመንግሥት ፕሮጀክቶች ከ30 በመቶ በላይ ለመስጠት በተወሰነው መሰረት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሪል ስቴት ገንቢዎችና ኮንክሪት ሚክስ የሚሰሩ ድርጅቶችም ቀጥታ ከድርጅቶች ምርቱን ማግኘት የሚችሉበት የአሰራር ሥርዓት መዘረጋቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ በኩንታል ዳንጎቴ 1 ሺህ 106 ብር ከ85 ሳንቲም፣ ደርባ 1 ሺህ 67 ብር ከ33 ሳንቲም፣ ሙገር 1ሺ 16 ብር ከ52 ሳንቲም፣ ካፒታል 1 ሺህ 26 ብር ከ35 ሳንቲም፣ ኩዩ በ1 ሺህ 65 ብር ሕብረተሰቡ ጋር እንደሚደርሱ ገልጸዋል፡፡
ሁሉም የሲሚንቶ ምርቶች ከ1 ሺህ 200 ብር በታች ለሕብረተሰቡ እንደሚቀርቡ ጠቁመው፣ በክልል እና ዞኖች የመሸጫ ዋጋ በቀጣይ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው የሲሚንቶ ሽያጭ መመሪያ መቀየሩን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።
የፋብሪካዎቹ የመሸጫ ዋጋ ለጊዜው ምርታማነት እስከሚጨምር ድረስ የፋብሪካ ዋጋ በስድስት ወር አንድ ጊዜ በሚኒስቴሩ እንደሚወሰንም ተገልጾ ነበር።
በተሻሻለው መመሪያ መሰረት የሲሚንቶ ሽያጭ ያለ ደረሰኝ እንዳይካሄድ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግ ሲሆን፤ በግብይቱ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድና ደረሰኝ ግዴታ ነው ተብሏል።