ቀጥታ፡

''በጉባዔው በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለን እንጠብቃለን'' የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

ሰመራ መስከረም 24/2011 በሐዋሳ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ኢህአዴግ )11ኛው ጉባዔ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው አንደሚጠብቁ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። ምሁራኑ ከኢዜአ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት ጉባዔው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ መሪነት የተጀመረውን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው ይጠብቃሉ። በዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት መምህር ደምሰዉ አምሳሉ ጉባዔው በሕዝብ  ጥያቄዎች ግፊት የመጣውን ለውጥና እየተወሰዱ ያሉትን ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ከጉባዔው እጠብቃለሁ ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የተጀመሩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን ለመተግበር የሚረዱ፣የአገርን ጥቅም የሚያስቀድሙና የሚያስከብሩ ውሳኔዎች እንደሚጠብቁም ገልጸዋል። አገራዊ የለውጥ ጉዞውን በጥርጣሬና በስጋት በማየት በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን የሚፈጥሩ ኃይሎችን ለመቆጣጠርና ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ መንግሥትና ህዝቡ በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታም ማስቀመጥም የውሳኔዎቹ አካል  ይሆናሉ ብለው እንደሚያምኑም አስታውቀዋል። የዩቨርሲቲዉ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር  መምህር እስጢፋኖስ ባለው በበኩላቸው ጉባዔው በእህት ድርጅቶች መካከል ሚዛኑን የጠበቀ ዴሞክራሲዊ ግንኙነት በመፍጠር በጋራ ለመልማትና የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች ይጠብቃሉ። በተጨማሪም የብሄር/ ብሄረሰቦችን ማንነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር በማጣጣም  ለአገራዊ አንድነት የሚበጅ አመለካከት የሚፈጥሩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እምነታቸውን  ገልጸዋል። ዜጎች በየትኛዉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው ተረጋግጠውላቸው የመኖር፣የመሥራትና ሃብት የማፍራት መብቶች የሚያስከብሩ ውሳኔዎችን ከጉባዔው ይጠብቃሉ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የዩኒቨርሲቲዉ ተቋማዊ ለውጥ ክፍል ባልደረባ አቶ ኢድሪስ ሰኢድ ጉባዔው ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን ለመዋጋት እንዲሁም  የጥላቻ ፖለቲካን ለማስወገድ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ይተላለፍበታል ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል። ከግል ጥቅም በላይ የአገርና የህዝብን ጥቅምና ክብር በተግባር በማስቀደም ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት የሚከፍሉ አመራሮች እንደሚመረጡ እምነታቸው መሆኑንም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) 11ኛ ድረጅታ ጉባዔውን ከትናንት ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ እያካሄደ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም