ቀጥታ፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ አምራች ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት ዘርፉን ያሳተፈ '' የኢትዮጵያ ታምርት'' የውይይት ፎረም እየተካሄደ ነው

ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ጥር 18/2015 በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር አምራች ኢንዱስትሪዎች እና አገልግሎት ዘርፉን ያሳተፈ '' የኢትዮጵያ ታምርት'' የውይይት ፎረም እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበርና ሌሎች የክልሉ አመራሮችና ባለሃብቶች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት የኔአባት በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በከተማዋ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ 111 ባለሃብቶች አሉ።

ከነዚህ መካከል 24ቱ ወደ ማምረት ሥራ ሲገቡ አራቱ የማሽን ተከላ ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች 20 ኢንቨስትመንቶች ግንባታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በቅድመ ግንባታ ላይ እና ግንባታቸውን ያቋረጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በኢንቨስትመንት የተሰማሩት ባለሃብቶች በሆቴል ቱሪዝም፣ በኮንስትራክሽን፣ በምግብ፣ በማኑፋክቸሪንግና መሰል ዘርፎች የተሰማሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በውይይት ፎረሙ ላይ ለ36 አልሚ ባለሃብቶች ከ54 ሄክታር በላይ መሬት ርክክብ እንደሚካሄድም ተገልጿል።

የ"ኢትዮጵያ ታምርት'' ፎረም በከተማው መካሄድ በኢንቨስትመንት ቦታ ተረክበው ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሃብቶች ፈጥነው እንዲገቡ መግባባት ላይ ለመድረስ እንደሚያግዝም ሃላፊዋ አመልክተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በባለሃብቶች በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን በተደራጀ አግባብ ምላሽ ለመስጠት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በአሁኑ ወቅት በከተማው ወደስራ የገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያመረቷቸው ምርቶች በርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃልና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች የተጎበኘ ሲሆን፤ አምራች ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት ዘርፉን ያካተተ ውይይትም መካሄድ ጀምሯል።

ከውይይት ፎረሙ በኋላም ወደሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴ ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም