የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የ745 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የ745 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 18/2015 የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የ745 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ዑስማን ዳዮኔ ተፈራርመዋል።
በድጋፍ የተገኘው ገንዘብም ለጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ለጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ተግባር የሚውል እንደሆነ ተገልጿል።
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በአየር ንብረት ለውጥና በግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል።
በዚህም 445 ሚሊየን ዶላሩ በተለይም በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች መሰረታዊና ፍትሕዊ የጤና አገልግሎት የሚውል ሲሆን ቀሪው 300 ሚሊዮን ዶላር ደግም የጎርፍ አደጋን የመከላከል ፕሮጀክቶች ይውላል ተብሏል።
ድጋፉ በጤናው ዘርፍ ፕሮጀክት ከ22 ሚሊየን በላይ ዜጎች እንዲሁም ለጎርፍ አደጋ መከላከል ፕሮጀክት በአየር ንብረት ተፅዕኖ ተጋላጭ የሆኑ 34 ሚሊዮን ዜጎች በተለይም ሴቶችና ህፃናትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የዓለም አቀፍ ልማት ማህበር በሚል ማዕቀፍ ድጋፉ የተደረገ ሲሆን በሶስተኛ ወገን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲዎች በኩል ይፈፀማል ተብሏል።